ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅ በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅ በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለጹት ለአንዲት ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሕዝብ ተደምረን በሠራነው የአረንጓዴ ዐሻራችን፣ ልምላሜ የተራቡ ተራሮች አረንጓዴ ለብሰዋል ብለዋል።

ምንጮች እና ተፋሰሶች ምድሩን አረስርሰዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በረሃማነት ይጸናባቸው የነበሩ ክበበ ምድሮች ነፋሻማ ሆነዋል ሲሉም ገልጸዋል።


 

የተፈጥሮን ጫና ተቋቁመናል! ይህ ደግ የተፈጥሮ ዕርቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል በመልዕክታቸው።

የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥን ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር በማስተሣሠር በተሠራው ሥራ የፍራፍሬ ተክሎች በስፋት ለምተዋል፤ ፍሬ መስጠትም ጀምረዋል ብለዋል።

ይህም በምግብ ራስን ለመቻል ለጀመርነው ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ተደማሪ ዐቅም ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ ልጆች ከፖለቲካ አሰላለፍ አልፈው፣ ከሐሳብ ተቃርኖ ተሻግረው፣ ገጸ ብዙ ልዩነቶችን አሸንፈው ለሀገርና ለትውልድ አስበው ያሳኩት የመተባበር ድል፣ የተጨበጠ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ልጆች ስንተባበር ትርፋችን እልፍ፣ ዕቅዳችንም የተሳካ የሠመረ ይሆናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ የእስከ ዛሬ ድካማችን መደምደሚያ፣ የድላችን መዳረሻ፣ በድል ላይ ቆመን ለሌላ የላቀ ድል የምንነሣበት ልዩ ዓመት ነው ብለዋል።

ሁላችንም በሩጫ ትግል ሊያልቅ ሲል እንደሚበረቱት ሊጠናቀቅ ሲል እንደሚፈጥኑት ጀግኖች አትሌቶቻችን ካለፉት ዓመታት አስበልጠን እንትከል! እንበርታ! እንፍጠን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም