ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ወቅታዊ እና አስተማማኝ የስታቲስቲክስ መረጃዎች እንዲመነጩ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ወቅታዊ እና አስተማማኝ የስታቲስቲክስ መረጃዎች እንዲመነጩ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ወቅታዊ እና አስተማማኝ መረጃዎች እንዲመነጩ፣ እንዲሰራጩና እንዲቀናጁ የሚያደርግ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩ ማር አባተ ገለጹ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅ 23/2018 ዙሪያ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩም ቋሚ ኮሚቴው ግልጽነትና ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አዋጅ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ወቅታዊ እና አስተማማኝ መረጃዎች እንዲመነጩ፣ እንዲሰራጩና እንዲቀናጁ የሚያደርግ ብሄራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በቦርድ እንዲመራ የሚደነግግ ሲሆን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲ አቅጣጫ ቁጥጥር የሚያከናውንበት እንዲሁም ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ አሰራርን በመከተል መረጃ ማመንጨት፣ መተንተንና ጥቅም ላይ እንዲውል ማስቻል ከዓላማዎቹ መካከል ይገኙበታል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ እንዳሉት፤ ረቂቅ አዋጁ በጥናት ላይ ተመስርቶ ተቋማትን ባቀናጀ አግባብ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
የብሔራዊ የስታቲስቲክስ ሥርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያስችል ጠቅሰው፥ ይህም የተቋማትን ሚናና ኃላፊነት በግልጽ የሚያስቀምጥ በመሆኑ የሥራ ድግግሞሽና መረጃ መፋለሶችን የሚያስቀር መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ጂኦስፓሻል፣ ዲጂታል፣ በሴንሰር ላይ የተመሰረቱ በመስኩ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥን ለማጎልበት አዋጁ ዓይነተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመረጃ አመንጪዎችን ሚስጥራዊነት መጠበቅ በረቂቅ አዋጁ በግልጽ የተቀመጠ ድንጋጌ ነው።
ከመረጃ ጥራት ጋር በተያያዘም ተቋማት የሚያመነጩት መረጃ ትክክለኛና መሰረታዊ መርህን ተከትለው መረጃ እንዲያመነጩ የአቅም ግንባታ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ከዓለም አቀፍና አህጉራዊ የስታቲስቲክስ መርሆና ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ረቂቅ አዋጁ በስታቲስቲክስ መስክ የሚከናወኑ ተግባራትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጸፈም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ የመረጃ ሰጪዎችን ማንነትና ሚስጥራዊነት መጠበቅ ለዘርፉ ሥራ መቃናት ቁልፍ ሚና አለው ያሉት ሰብሳቢው በአዋጁ የመረጃ አመንጪዎች ግለሰቦችና ተቋማት ሚስጥራዊነት መጠበቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።