አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በተሠራው ሥራ የሕክምና ተቋማት አቅምና ዘመናዊነት እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በተሠራው ሥራ የሕክምና ተቋማት አቅምና ዘመናዊነት እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤናው ዘርፍ ባከናወናቸው መጠነ-ሰፊ የልማት ሥራዎች የሕክምና ተቋማት አቅምና ዘመናዊነት እያደገ መምጣቱን የከተማዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የላፍቶ ሆስፒታልን በቅርቡ በመረቁበት ወቅት፤ የሀገሪቱን የጤና ፖሊሲ ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያን ቀዳሚ የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተሰነቀውን ትልቅ ራዕይ ከግብ ለማድረስ እንደ አንድ ትልቅ የአሸጋጋሪ ምዕራፍ ተጠቃሽ መሆኑን መግለጻቸው ይታወቃል።
ይህም ዜጎች ለላቀ የህክምና አገልግሎት ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገር በሚጓዙበት ወቅት የሚባክነውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ የሚረዳ ሲሆን፤ የዘርፉን የአገልግሎት ጥራትም ወደ አዲስ ከፍታ ያሸጋግረዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የህክምና ማዕከልነት ሚና ይበልጥ እንደሚያጎላውም መግለጻቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከአዳዲስ ሆስፒታሎች ግንባታ እስከ ዲጂታል የጤና መረጃ ሥርዓት ዝርጋታ የተከናወኑ ተግባራት አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተያዘው ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ አካል ናቸው።
በከተማዋ የዘመናዊ ሕክምና አቅምን ከሁለት እጥፍ በላይ ያሳደገ ታሪካዊ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ዘጠኝ አዳዲስ ዘመናዊ ጤና ጣቢያዎች ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን፤ በዚህም ከዚህ ቀደም የጤና ተቋም ያልነበራቸውን አምስት ወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በ40 ነባር የጤና ጣቢያዎች ላይ ሰፊ የማስፋፊያና የማጠናከሪያ ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው ያብራሩት።
ዘውዲቱ መታሰቢያ፣ ራስ ደስታ ዳምጠው እና ዳግማዊ ምኒሊክን ጨምሮ ነባር ሆስፒታሎች ታድሰዋል፤ አዳዲስ ማስፋፊያ ሕንጻ ተገንብቶላቸዋል ያሉት ኃላፊው፤ የአገልግሎት አቅማቸውም በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ተደርጓል ብለዋል።
በጤና መሠረተ ልማት ረገድ ከተመዘገቡት ስኬቶች መካከል የአበበች ጎበና እናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ግንባታ በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ የእናቶችና ሕጻናት ሞት ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ፣ በዘላቂ ልማት ግቦች ሥር የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ መለኪያ ካቀደችው ጊዜ አስቀድማ ማሳካቷንም ነው ያነሱት።
በከተማዋ የሕክምና ጥራትንና የቴክኖሎጂ አቅምን ዓለም ከደረሰበት ደረጃ የሚያደርሱና ለውስብስብ የሕክምና ዓይነቶች በራስ አቅም አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ልዩ የሕክምና ልህቀት ማዕከላት ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ሁሉም ሆስፒታሎች የራሳቸውን ኦክስጅን በማምረት ቀደም ሲል በሲሊንደር አቅርቦት ላይ የነበረባቸውን ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ አስቀርተዋል ብለዋል።
የአገልግሎት ፍጥነትን፣ ወጥነትንና የመረጃ አያያዝን ለማዘመን በተከናወነው ሥራ፤ ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ 67 የጤና ተቋማት በዲጂታል የሕክምና መረጃ ሥርዓት ውስጥ መካተታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በመንግስት ድጋፍና ምቹ ሁኔታዎች በመታገዝ የግል ባለሀብቶችም በጤናው ዘርፍ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን በማቋቋም ለአገልግሎት ማብቃት መቻላቸውን ገልጸዋል።