ቀጥታ፡

የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከዛሬ ጀምሮ በተሳካ ሁኔታ እየተሰጠ ነው-የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦የ6ኛ ክፍል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ በተሳካ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገለፁ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰኔ 8 እስከ ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚሰጠው የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ ባሉ 767 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 85 ሺህ 17 የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ።


 

የፈተናውን ሂደት የሚከታተሉ 3 ሺህ 400 የፈተና አስፈጻሚዎች በከተማዋ በሚገኙ በ199 የፈተና ጣቢያዎች  መመደባቸውንም ገልጸዋል።

ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን አንስተው በፈተና ጣቢያዎች አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ፈተናው መጀመሩን ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች በተደረገው ምልከታ በመፈተኛ ጣቢያዎች ለተማሪዎች በራስ መተማመን የሚፈጥር ዐውድ መኖሩን ተመልክተናል ብለዋል። 

ተማሪዎች ታዳጊዎች  በመሆናቸው በስነልቦና ለማዘጋጀት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የተማሪዎችን በራስ መተማመን ለማሳደግና ኩረጃን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸውንም አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም