ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ ሀገራዊ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብን ለማሻሻል ወሳኝ መሰረት የሚጥል ነው- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦ረቂቅ አዋጁ ሀገራዊ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብን ለማሻሻል ወሳኝ መሰረት የሚጥል መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅ ሰሙ ማሞ ገለጹ፡፡  

የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት መድረክ አካሒዷል፡፡


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የአዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ባቀረቡት ገለጻ፤ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብ የምግብን ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ ያለውን አጠቃላይ ሰንሰለት የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ ዜጎች በልዩ ልዩ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ ምግብ እንዲያገኙ በማስቻል ጤናማ እና አምራች ትውልድ ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክት አመላክተዋል፡፡


 

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እንደ መነሻ በመውሰድ የተዘጋጀው ይህ አዋጅ፥ ዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕግ እንዲመራ ከማስቻሉም በላይ የተቋማትን ቅንጅታዊ ሥራ ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡ 

በመድረኩ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተወካይ ገነት ስዩም፤ የነገ ሀገር ተረካቢ ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ረቂቅ አዋጁ ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር አሻግረው ዘውዱ(ዶር) በበኩላቸው፤ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብ በህግ እንዲመራ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በረቂቅ አዋጁ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አንቀጾች መካተቱን ያደነቁት ደግሞ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን የመጡት አዳነች መለስ ናቸው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅ ሰሙ ማሞ፤ ረቂቅ አዋጁ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብን በሕግ በመምራት ሀገር እና ትውልድ የሚገነባበት ነው ብለዋል፡፡

የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት በሀገራችን የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብን ለማሻሻል ወሳኝ መሰረት እንደሚጥል ገልጸዋል፡፡

 


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም