ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችን በማስቀጠል የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ

ባህር ዳር፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ከተማ በማህበረሰቡ ተሳትፎ የሚከናወኑ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችን በማስቀጠል የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ። 

የባህር ዳር ከተማ አመራሮች የተሳተፉበት በልማትና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት ባህርዳርን በመሰረተ ልማት በማዘመን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በማህበረሰቡ ተሳትፎ የከተማዋን ሰላምና ልማት በማጠናከር የህዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል። 

በተለይም የከተማዋን ማህበረሰብ በማሳተፍ የተከናወኑ የሰላምና የህግ ማስከበር ሥራዎች ለሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠሩ ገልጸዋል።


 

የሰላሙ መጠናከር የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የስማርት ሲቲ ትግበራ እና ሌሎች ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን አስችሏል ብለዋል።

ይህም ከተማዋን ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ፣ ለቱሪዝምና ለኑሮ ምቹ በማድረግ የነዋሪውን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ማህበረሰቡም በጠቅላላ ምርጫው ድምጹን ከመስጠት ባለፈ ለምርጫው ሰላማዊነትና ስኬት ያደረገው አስተዋጽኦ ለሰላምና ልማት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።

በቀጣይም ህዝቡ በከተማዋ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ላይ የሚያደርገውን ንቁ ተሳትፎ በማሳደግ ለዘላቂ የብልጽግና ጉዞ የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል።

የከተማ አስተዳደሩም በቀጣዮቹ 90 ቀናት የክረምት ሥራዎችን በላቀ ደረጃ በመፈጸምና የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት በጊዜ የለኝምመንፈስ ሊሰራ እንደሚገባ ምክትል ከንቲባው አሳሰበዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ሃላፊ አቶ ጊዜው ታከለ እንዳሉት፣ በየደረጃው ያለው አመራር ዋነኛ ትኩረቱ ህዝብን በሰላምና በልማት ተጠቃሚ ማድረግ ነው።

ለዚህም ህዝባዊነትን በመላበስ ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ተአማኒነት ያለው አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ላይ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና የክፍለ ከተሞች አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም