ቀጥታ፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ለ500 ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ሰጠ

አምቦ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ለ500 ያህል ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና አገልግሎት መስጠቱን ገለጸ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አበበ መገርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ ባለፉት አራት ቀናት የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና አገልግሎትን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን አዘጋጅቷል። 


 

በዚህም እንቅስቃሴ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ህክምናውን ፈልገው የመጡ 500 ሰዎች ህክምናውን በነጻ ማግኘት ችለዋል ብለዋል።

በዘመቻው የአምቦ ከተማን ጨምሮ የጀልዱ፣ የድሬ ኢንጪኒ፣ የአደአ በርጋና የቶኬ ኩታዬ ወረዳ በበሽታው ተይዘው የነበሩ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። 

የተሰጠው የህክምና አገልግሎት በገንዘብ ሲሰላ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።


 

በሆስፒታሉ የዓይን ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ጉዲና ሚሊኬሳ በበኩላቸው፤ በሽታው የሚከሰተው በአብዛኛው ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ እንደሆነ ገልጸዋል። 

በህክምና ዘመቻው በተደረገው ርብርብ የብዙዎችን ብርሃን መመለስ ተችሏል ያሉት ኃላፊው፤ ህብረተሰቡ በሽታው እንደተከሰተ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ በወቅቱ መታከም እንደሚገባው አመልክተዋል።

የዓይን ሞራ ግርዶሽ የግልና የአካባቢ ንጽህናን ካለመጠበቅም ሊከሰት የሚችል በመሆኑ፣ ማህበረሰቡ የራሱንና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊከላከለው እንደሚገባም ዶክተር ጉዲና አሳስበዋል።

በነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ዘመቻ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ከአደአ በርጋ ወረዳ የመጡት አቶ ዱጉማ ደሜ፤ ለስድስት ዓመታት በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ማየት ተስኗቸው መቆየታቸውን ገልጸው፣ በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ህክምና ማየት እንደቻሉ ተናግረዋል። 

ከኢንጪኒ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ቢሪቱ ኮርሳ በበኩላቸው፤ የህክምና አገልግሎቱን ማግኘት ባለመቻላቸው ለሦስት ዓመታት ማየት ተስኗቸው መቆየታቸውን ተናግረው፣ ከዚህ ችግር ለታደጓቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ለተመሳሳይ ችግር ተዳርገው የነበሩት የኤጄሬ ወረዳ ነዋሪው አቶ ጎዳ ሻንኩራ፤ በተደረገላቸው ህክምና እይታቸው በመመለሱ ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስም ሆነ ለመሥራት ዕድል በማግኘታቸው ደስታቸው ድርብ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም