ቀጥታ፡

በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረጉ ማበረታቻዎች አመርቂ ውጤት አምጥተዋል -ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

አገና፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረጉ ማበረታቻዎች አመርቂ ውጤት ማምጣታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የተገነባው ቪታሳሉቲ የላሜራና ቱቦላሬ ብረት ፋብሪካን መርቀዋል።

በእዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪው መስክ ባለሀብቶችን በብዛት ለመሳብ በትኩረት እየተሰራ ነው።


 

በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ለማበረታታት በቦታ አቅርቦት፣ በመሰረተ ልማት፣ በገንዘብ ብድር እና ሙያዊ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸው፤ ይህም ለዘርፉ ውጤታማነት የራሱን አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በሚደረጉ ማበረታቻዎች ምርትን በሚፈለገው ልክ የሚያቀርቡ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎችን ከመገንባት ባለፈ ተኪ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ መጥተዋል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ በዞኑ በተኪ ምርት ላይ የተሰማራ የመጀመሪያ ግዙፍ ፋብሪካ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአካባቢው በተለያዩ የኢንቨስትመት ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ቦታዎች መዘጋጀታቸው በባለሃብቱ ተመራጭ አድርጎታል ያሉት ደግሞ የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ ናቸው።

ፋብሪካው ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።

የቪታሳሉቲ የላሜራና ቱቦላሬ ብረት ፋብሪካን ባለቤት አቶ ሰዒድ ሃጂ ኑሩ፤ ዘርፉን ለማሳደግ የተሰጠው ትኩረት እና የተመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ለፋብሪካው ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸው፤ በሙሉ አቅሙ ወደስራ ሲገባ ለ123 ቋሚ እንዲሁም ለ273 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም