ቀጥታ፡

በዞኑ ማህበረሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥና የልማት ስራዎችን የማስቀጠል ተግባራት ይጠናከራሉ

መተማ፣ ሰኔ 8/2018  (ኢዜአ):-በምዕራብ ጎንደር ዞን ማህበረሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን የማስቀጠል  ተግባራትን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ የዞኑ አመራሮች ገለጹ።

የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ከየወረዳው ከተወጣጡ አስተዳዳሪዎችና ከንቲባዎች ጋር በወቅታዊ የፀጥታና የልማት ስራዎች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሄደዋል። 

በወቅቱም ​የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ እያሱ ይላቅ  እንደገለጹት፤ በዞኑ ላለው ለውጥ፣ ዕድገትና አስተማማኝ ሰላም ዋነኛው ባለቤትና አጋዥ  ህብረተሰቡ ነው። 

ዞኑ ሰፊ የኢንቨስትመንት እና የልማት ቀጠና መሆኑን ጠቅሰው የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ ለሀገር ኢኮኖሚም ጭምር ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል። 

"ባለፉት ጊዜያት ከህዝባችን ጋር በመቀናጀት በርካታ ፈተናዎችን ማለፍ ችለናል" ያሉት አስተዳዳሪው፣በቀጣይም ይኸው ህዝባዊ ትስስር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። 

የአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እሸቴ ሙላው እንዳሉት፤ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን ከህዝቡ ጋር መወያየትና አብሮ መስራት ይጠበቃል። 

አርሶ አደሩ ያለምንም ስጋትና በነፃነት ምርቱን ማምረት እንዲችል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል። 

ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር ያለውን ሰላማዊ ትስስር ለማጥበቅና የወንጀል ድርጊቶችን በጋራ ለመግታት ከህብረተሰቡ የሚገኘው ጥቆማና ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰራም አንስተዋል። 

የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ግዛት ሰረፀ በበኩላቸው፣ ወረዳው በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ፣ ሰፊ የእርሻ መሬት ያለበት በመሆኑ ይህን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ሰላምን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም በየቀበሌው ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር የፀጥታ ስጋቶችን በጋራ የመከላከል ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

​በዞኑ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰሩም አመራሮቹ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም