ቀጥታ፡

የጅማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የስራ ተነሳሽነትን አሳድጓል

ጅማ፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦ በጅማ ዞን የሚገኙ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት፣ ለማህበረሰቡ እየሰጡት ካለው ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በተጨማሪ የአገልጋዮችን የስራ ተነሳሽነት ማሳደጋቸው ተገለጸ።

ማዕከላቱ በብቁ ባለሙያዎች መደራጀታቸውና ዘመናዊ አሰራርን መከተላቸው ለአገልጋዩም ሆነ ለተገልጋዩ ትልቅ እረፍት መሆኑ ተመላክቷል።


 

የሊሙ ገነት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሙያዎች ሪዳ ከማል እና አዳል ኃይለማርያም፤ በማዕከሉ ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት የስራ ተነሳሽነት እንደጨመረላቸው ገልጸዋል።


 

ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የተደራጀ በመሆኑ የአገልግሎት ፍጥነቱን ከመጨመሩ በላይ የሰራተኛውንም ሆነ የህብረተሰቡን ውድ ጊዜ መቆጠብ አስችሏል።

በተመሳሳይም የጅማ ማዕከል ባለሙያዎች አብዱልኑራ አባተማም እና ሰሚራ ሐሰን በበኩላቸው፣ ምቹ የስራ ቦታ መፈጠሩ ያለምንም የተገልጋይ ቅሬታ ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።


 

ሌላው በዞኑ በቅርቡ አገልግሎት በጀመረው የኦሞ ናዳ ወረዳ አሰንዳቦ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል በማገልገል ላይ የሚገኙት ማረሜ በቀለ እና አንዋር አባዲጋ፣ ለማህበረሰቡ በንቃትና በትጋት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ምቹ የስራ ሁኔታ መኖሩ ሰራተኞች ያለመሰልቸት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ማድረጉን የጠቀሱት ባለሙያዎቹ፣ በዚህም ለዓመታት የህብረተሰቡ የቆየ ጥያቄ የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሙሉ በሙሉ መቀረፉን አስታውቀዋል።

በማዕከላቱ አገልግሎት ለማግኘት የመጡት ሙስጠፋ አብዱረህማን በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው እንዲህ ያለ ዘመናዊ ማዕከል መከፈቱ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ ገና ወደ ማዕከሉ ስገባ ከመስተንግዶው ጀምሮ የባለሙያዎቹ አቀባበልና ፍጥነት ከፍተኛ እርካታ የሚሰጥ ነው ብለዋል።


 

ለመንጃ ፈቃድ አገልግሎት የመጣው ጀማል አብዱረህማንም ማዕከሉ ከምንም በላይ ወደ ህብረተሰቡ የቀረበና ለዓመታት ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግሯል።

በጅማ ከተማ በሚገኘው ማዕከል የልደት ካርድ ለማውጣት የመጣችው የጅማ ከተማ ነዋሪ ቤተመቅደስ አምሀ፣ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ማግኘቷ እንዳስደሰታት ገልጻለች።


 

የጅማ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ጀማል ሳሊ፣ በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ለተገልጋዩ ብቻ ሳይሆን ለአገልጋዮችም ጭምር የእርካታ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ህብረተሰቡ ጊዜና ገንዘቡን ቆጥቦ ፈጣን አገልግሎት አግኝቶ መመለሱና በተሰጠው አገልግሎት ረክቶ የሚሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ለሰራተኛው ትልቅ ተነሳሽነት መፍጠሩን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም