ቀጥታ፡

በሕጻናት ትምህርትና ጤና ላይ መስራት የነገዋን የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ያስችላል - ትምህርት ሚኒስቴር

ድሬደዋ፣ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፡- በሕፃናት ትምህርትና ጤና ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ለነገዋ የበለፀገች ሀገር መሠረት እየጣሉ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በድሬደዋ የተገነባው" ኡሚ" አስተዳደር አቀፍ የትምህርት ቤት የምገባ ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ወደ አገልግሎት ተሻግሯል።


 

በምረቃው ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩት አጠቃላይ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተካሄዱ ይገኛሉ። 

እነዚህ ተግባራትም በሕፃናት ትምህርትና ጤና ላይ እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች ጋር ተዳምረው፣ የነገዋን የበለፀገች ሀገር የመገንባት ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በቅንጅታዊ ስራ አበረታች ውጤት ከመጣባቸው መርሃግብሮች መካከል አንዱ የትምህርት ቤቶች ምገባ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመርሃግብሩ እየተተገበሩ ባሉ የተቀናጁ ተግባራት አማካኝነት ሕፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙና ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ፤ የትምህርት ጥራትን በማጎልበትና የተማሪዎችን የጤናና የአመጋገብ ሥርዓት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም አሠራሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወላጆች የኢኮኖሚ ጫና በእጅጉ እየቀነሰ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።

በድሬደዋ ዛሬ የተመረቀውና ወደ ስራ የገባው ማዕከል የተጀመረውን የትምህርት ቤቶች ምገባ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው ለስራው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች የምገባ ኢንሼቲቭ  ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬአለም ሽባባው በበኩላቸው በድሬደዋ በጥራትና በፍጥነት የተገነባው ኡሚ የምገባ ማዕከል ለሀገራችን በምሳሌነት የሚጠቀስና ተስፋፍቶ የሚቀጥል ነው ብለዋል።

ዘመናዊ የምገባ ማዕከላትን በማስፋት በህጻናት ላይ በትኩረት መስራት ለሀገር ከፍታና ብልፅግና መረጋገጥ መሠረታዊ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ ህፃናት ላይ የሰራ ሀገር በዘላቂ  ከፍታ መጓዙን ማረጋገጫ መንገድ ነው ብለዋል።

የትምህርት ቤቶች ምገባ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ እና የትምህርት መጠነ ማቋረጥን በመከላከል ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ያሉት ደግሞ የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው።


 

መርሃ ግብሩ ዘርፈ ብዙ ለውጦች እየተመዘገቡበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ሰዓት በመንግስትና በአጋር አካላት ትብብር በአስተዳደሩ በ42 ትምህርት ቤቶች ምገባ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው ማዕከል የተጀመረውን ስራ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚያስችል በመግለፅ።


 

የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልዪ በበኩላቸው ማዕከሉ በተለያዩ አጋር አካላት በተበታተነ መንገድ ሲካሄድ የነበረውን የትምህርት ቤት ምገባ  ተቋማዊ እና ወጥ በሆነ መንገድ ለመካሄድ ያስችላል ብለዋል።

በ18 ሄክታር መሬት የተገነባው ኡሚ የምገባ ማዕከል በመጀመሪያ ምዕራፍ  አምስት ሺህ ተማሪዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለማዋልም ዝግጁ ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም