"ቤጉ መሶብ" አዳዲስ አገልግሎቶችን በማካተት ተደራሽነቱን እያሰፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"ቤጉ መሶብ" አዳዲስ አገልግሎቶችን በማካተት ተደራሽነቱን እያሰፋ ነው
አሶሳ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ (ቤጉ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አዳዲስ አገልግሎቶችን በውስጡ በማካተት ለተገልጋዮች ያለውን ተደራሽነት እያሰፋ መሆኑ ተገለጸ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እያደገ የመጣውን የንግድ፣ የግብርና እና የኢንቨስትመንት ፍላጎት ለማስተናገድ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ለማዘመን በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በአምስት የክልል እና ሶስት የፌደራል ተቋማት 33 አገልግሎቶችን አካቶ ስራ የጀመረው "ቤጉ መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱን በማስፋት ተደራሽነቱን እያሳደገ ይገኛል።
የቤጉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር ኢንጂነር ሰመረ ጅራታ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት 33 የነበሩትን አገልግሎቶች ወደ 42 በማሳደግ ዜጎች ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ ነው።
ፍትህ ቢሮ እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በማዕከሉ እየሰጧቸው ከሚገኙ አገልግሎቶች በተጨማሪ ውልን መርምሮ ማጽደቅ እና የመድን ፈንድ አገልግሎት መስጠትን የመሳሰሉ አዳዲስ የስራ ዘርፎችን በማካተት የተገልጋዮችን እርካታ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በቅርቡም የክልሉ ማዕድን ቢሮን ጨምሮ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና ሌሎች ተቋማት ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ቤጉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እስካሁን ድረስ ከ28 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት መስጠቱን ጠቁመው፤ የተገልጋዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ቤጉ መሶብ በቅርቡ ስራ ለጀመረው አሶሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም አስፈላጊውን የሙያ ዕገዛ በማድረግ ማዕከሉ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉን አብራርተዋል።
በቅርቡም በባምባሲ፣ ግልገል በለስ እና ካማሽ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።