ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን የመገንባት ሂደት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው

ባህርዳር፤ ሰኔ 8/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስፈን የሚያስችል የፀጥታ ኃይል እየተገነባ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለፁ።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ደህንነት አፈፃፀምን የሚገመግምና በቀጣይ ሁለት ወራት በሚከናወኑ ተግባራት ዕቅድ ዙሪያ የሚመክር መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን የመገንባት ሂደት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።

ባለፋት ጊዜያት የፀጥታ ሃይሉ በተቀናጀ መንገድ በተሰራ ህግ የማስከበር ተግባር በክልሉ ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልፀዋል።

በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙና የክልሉን ብሎም የሀገሪቱ ሰላም መሆን የማይዋጥላቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች የክልሉን ብሎም የሀገርን ሰላም አደጋ ላይ ለመጣል የተደረገውን ሙከራ ማክሸፍ እንደተቻለ አንስተዋል።

በተለይም እነዚህ የህዝብና የሀገር ጠላት የሆኑ ፅንፈኛ ቡድኖች ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ በተቀናጀ መንገድ ያደረጉትን ጥረት የፀጥታ ኃይሉ በላቀ ብቃት ማምከን መቻሉን ተናግረዋል።


 

ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አባላት በጥምረት በሰሩት ስራም ምርጫው እንዳይካሄድ የተደረጉ ሙከራዎችን ሙሉ በሙሉ በማክሸፍ ምርጫው በስኬት እንዲከናወን ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ህዝባዊነትን በተላበሰ መንገድ ባካሄደው ርብርብም ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ሊፈፀም የታሰበን አጥፊ ድርጊት ሊያመክን እንደቻለም አክለዋል።

ምርጫው በስኬት እንዲከናወን የፀጥታ ኃይሉ ለተወጣው ኃላፊነት አመስግነው፤ በቀጣይም ሰላምን የማስጠበቁ ተግባር በላቀ ቁርጠኝነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የተቋሙ አመራሮች እየተሳተፋ ሲሆን የምርጫ ደህንነት አፈፃፀምና የቀጣይ ሁለት ወራት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም