ቀጥታ፡

አገልግሎቱ አሰራርን ከማዘመን ባለፈ  የተገልጋይ እርካታን የሚያሳድግ ነው

ወልቂጤ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰራርን ከማዘመንና ከማቀላጠፍ ባለፈ የአገልጋይነት ባህልን በማዳበር የተገልጋይ እርካታን የሚያሳድግ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)  ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )በወልቂጤ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅቱ እንዳሉት፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስት ተቋማትን አሰራር ከማዘመን ባለፈ የአገልጋይነት ባህል በመገንባት የተገልጋይ እርካታን የሚያሳድግ ነው።

ለዚህም የአገልግሎት አሰጣጡን በየጊዜው በማዘመንና ተግባሩን በማጥናት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትኩረት መሰጠቱን  አብራርተዋል።

በክልሉ ሦስት ማዕከላት ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው በክልሉ የመንግስት አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀደም ሲል በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋለውን እንግልት በመቀነስ እርካታን እንደሚያመጣ ጠቁመዋል።


 

በማዕከሉ ሰባት የፌደራልና የክልል ተቋማት 41 የተለያዩ የአገልግሎት አይነቶችን እየሰጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ናቸው። 


 

በቴክኖሎጂ የተደራጀው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከዚህ ቀደም ረጀም ቀናትን ይፈጅ የነበረውን ጉዳይ በአጠረ ጊዜ በመጨረስ ፈጣን ምላሽን ይሰጣል ብለዋል።

በክልሉ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የወልቂጤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሆሳዕናና በወራቤ ከተሞች ከተገነቡት ቀጥሎ  ሦስተኛው መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም