የሀሳብ ልዩነቶችንና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የስልጡንነት መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀሳብ ልዩነቶችንና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የስልጡንነት መገለጫ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦የሀሳብ ልዩነቶችንና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የስልጡንነት መገለጫ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ቆይተው በሰላማዊ መንገድ ወደ ማህበረሰቡ ከተቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ጋር በአዳማ ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የቀድሞ ታጣቂዎቹ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ የወሰኑትን ውሳኔ አድንቀዋል።
የሀሳብ ልዩነቶችንና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የስልጡንነት መገለጫ ነው ያሉ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሰላም መመካከርና መነጋገር ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚያካሂድ መግለጹ ይታወቃል።
ለዚህም በተለያዩ ምዕራፎች ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል አሳታፊና አካታች የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ሥራ ማከናወኑም ይታወቃል።
ኮሚሽኑ በክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ በወረዳዎች እንዲሁም በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ ማካሄዱም አይዘነጋም።