በሐረር የተከናወነው የኮሪደር ልማት ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ የሚያሻግር ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር የተከናወነው የኮሪደር ልማት ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ የሚያሻግር ተግባር ነው
ሐረር፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረር ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ የሚያሻግር ተግባር መሆኑን በከተማዋ የሚኖሩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ገለጹ።
ሐረር በተለይም ጥንታዊቷ የጀጎል ግንብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበባት ታሪካዊና ባህላዊ የቅርስ መናኸሪያ ናት።
ይህንን ህያው ታሪክና ጥንታዊ ይዘት ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ደግሞ የክልሉ ብቻ ሳይሆን የሀገር አቀፍ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የተጀመረውና አሁን ላይ በሐረር ከተማ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ዋና ዓላማም የከተማዋን መሰረተ ልማት ማዘመን፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና ከተማዋን ለቱሪስት መስህብ ይበልጥ ምቹ ማድረግ ነው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማዋን ታሪካዊ ቅርሶች በጠበቀና በተንከባከበ መልኩ የተሰራ በመሆኑ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ትልቅ አሻራ ማሳረፉን ገልጸዋል።
"ውልደቴና እድገቴ ጀጎል ነው" ያሉን 80 ዓመት እድሜ ባለፀጋ አቶ መሀመድ ዩስፍ ቀደም ሲል ጀጎልን ጨምሮ ሌሎች በውስጡ የሚገኙ ቅርሶች በቆሻሻና በተለያዩ ምክንያት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
ኮሪደር ልማቱ ቀደም ሲል የታዩ ችግሮችን የታደገ፣ ለአዛውንቶችና ህጻናት ማረፊያና መዝናኛ የፈጠረ፣ የሐረርን ቀደምት ስልጣኔና ታሪክ በሚመጥን መልኩ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
"ሐረር አሁን ነው የደመቀችው፤ በከተማው በገጠሩና በጀጎል የተሟላ የኮሪደር ልማት ስራ ተከናውኗል" ያሉት ደግሞ አባገዳ አህመድ ዩስፍ ናቸው።
የኮሪደር ልማቱ ልጆች በአግባቡ እንዲጫወቱ ምቾት ከመፍጠር ባለፈ መንፈስን የሚያድስ አብሮነትና አንድነትን ያጠናከረ ገጸ በረከት ስለማበርከቱ አንስተዋል።
ወይዘሮ እጸገነት ውቤ በበኩላቸው፤ ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ የኮሪደር ልማት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
መንግስት በከተማም ሆነ በገጠር ያከናወናቸውን ስራዎች ሐረር የቱሪስት መዳረሻዎቿ እንዲጎለብቱ ከማስቻሉ ባለፈ ለሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ ስራ እየጠፋች የነበረችውን ሐረርን የመለሰና ለስራና ለመዝናኛ ምቹ የሆነችውን ሐረርን ያሳየን ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ መሊካ ዘከሪያ ናቸው።
የኮሪደር ልማት ስራው የብስክሌት፣ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገድን ያካተተ በመሆኑ ለእግረኛና ለተሽከርካሪ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው ብለዋል።
የከተማውን ውበት ከማጉላት ባለፈ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚረዱ መሰረተ ልማቶችም የተዘረጉባት መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ የኮሪደር ልማት ስራ ባህልና ቅርስን በጠበቀ መልኩ ስለመከናወኑ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ ረዒስ ዩስፍ ናቸው።
ተቋማትንና ህብረተሰቡን በማስተባበር በጀጎል ውስጥ እና ዙሪያው እንዲሁም በከተማው የኮሪደር ልማት ስራው መከናወኑን አንስተዋል።