በክልሉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል
ባህርዳር፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የሰው ኃይል አቅም ግንባታን በማጠናከር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዙሪያ ለሚዲያና ህዝብ ግንኙነት አመራሮች ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የቢሮ ሃላፊዋ ወይዘሮ ባንች አምላክ ገብረማርያም በመድረኩ እንደገለፁት፤ የመንግስት አገልግሎትን ፈጣንና ተደራሽ በማድረግ የህዝብ እርካታን ለመፍጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በአራት ከተሞች በማስጀመር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገብተው ተገልጋዩን እያስተናገዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱን አሁን ስራ ከጀመሩት ባህር ዳር፣ ደሴና ወልዲያን ጨምሮ ወደ 38 ከተሞች ለማስፋት የግንባታና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራ በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዚህም እስከ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን በማጠናቀቅ ከሃምሌ ወር ጀምሮ ወደ ተሟላ ትግበራ እንደሚገባም አስረድተዋል።
በቀጣይም ተከታታይነት ያለው የሰው ሃይል አቅም ግንባታ ተግባራትን በማከናወን ሪፎርሙን የማፅናት ስራ ይሰራል ብለዋል።
ይህም በስነ ምግባሩ የተመሰገነ፣ በእውቀትና ክህሎት የበለፀገና ህዝባዊነትን በመላበስ ቁርጠኛ የሆነ ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት በመንግስት አገልግሎት ላይ የህዝብ እርካታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዛሬው መድረክም የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት አመራሩና ባለሙያው በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ ተግባራትን ተገንዝቦ ለህዝብ በማሳወቅ ሪፎረሙ ዳር እንዲደርስ ለማስቻል ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል።
በመድረኩ የተቋማት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እና የተለያዩ የሚዲያ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን በሪፎርሙ ዙሪያ የመወያያ ፅሁፋ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።