ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ተሳትፎ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚካሄደው የማጠቃለያ የምክክር ጉባኤ መላው ሕዝብ ከጎኑ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኮሚሽኑ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በሕዝባዊ ውይይት ሰብስቧል፡፡

በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምክረ ሀሳብ የሚያሰናዳበትን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።

ስለሆነም ኮሚሽኑ መላው ኢትዮጵያውያን ለዚህ ታሪካዊ ሁነት መሳካት ከጎኑ በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም በዚህ ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የተመረጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የባለድርሻ አካላት ወኪሎች ውጤታማ ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችላቸውን ሁለንተናዊ ዝግጅት እያደረጉ እንዲጠብቁ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም