ግብጽ ከቤልጂየም፤ ኬፕቨርዴ ከስፔን የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ ከቤልጂየም፤ ኬፕቨርዴ ከስፔን የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ 23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል።
በምድብ ሰባት ቤልጂየም ከግብጽ በሲያትል ስታዲየም ምሽት አራት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
አውሮፓዊቷ ሀገር ቤልጂየም በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የአሁኑ ለ15ኛ ጊዜ ነው።
ቤልጂየም በመድረኩ ትልቁ ውጤቷ እ.አ.አ በ2018 በሩሲያ በተካሄደው 21ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው።
ተጋጣሚዋ ግብጽ በዓለም ዋንጫ አራተኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።
የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ከምድብ አልፋ አታውቅም።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አራት የወዳጅነት ጨዋታዎች ግብጽ ሶስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ቤልጂየም አንድ ጊዜ ድል ቀንቷታል።
የሀገራቱ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በምድብ ስምንት ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ስፔን ከኬፕቨርዴ በአትላንታ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በዓለም ዋንጫው 17ተኛ ተሳትፎዋን የምታደርገው ስፔን እ.አ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 19ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አሸናፊ በመሆን ብቸኛ ድሏን ማሳካት ችላለች።
አፍሪካዊቷ የደሴት ሀገር ኬፕቨርዴ በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዚሁ በምድብ ስምንት ሳዑዲ አረቢያ ከኡራጓይ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በሚያሚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሌላ በኩል በምድብ ሰባት ኢራን ከኒውዝላንድ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በሎስ አንጀለስ ስታዲየም ይጫወታሉ።