የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር
በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም ባሳለፍነው ሳምንት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
👉የተራሮች ስር ፈርጥ - ወልዲያ
የዛሬው የወፍ በረር ምልከታችን የሚጀምረው የተራሮች ስር ፈርጥ በሆነችው ወልዲያ ከተማ በመገኘት ነው። ከደሴ በ120 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውና በረጃጅም ተራሮች የተከበበችው ወልዲያ ከተማ ከነበረችበት ጉስቁልና ወጥታ አሁን ላይ በውበት ፈክታ ትገኛለች።
በሳምንቱ በዚህች ከተማ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የኮሪደር ልማቷንና የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሁም ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀዋል፤ ተዘዋውረውም ጎብኝተዋል።
በተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ትውፊቶች ስሟ ጎልቶ የሚጠራው ወልዲያ እንደ ከዋክብት ፈክታ እንግዶቿን ተቀብላ አስተናግዳለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ወደ ገጠር ጭምር እየተስፋፉ መሆኑን አንስተው በቀጣይ ኢትዮጵያ ዕዳዎቿን እያራገፈች ተስፋዎቿን እየጨበጠች ትገሰግሳለች ብለዋል።
👉የሸደር አዳሪ ትምህርት ቤት
የሚቀጥለው መዳረሻችን በሶማሊ ክልል ፋፈን ዞን አውበሬ ወረዳ ሼደር ከተማ አዲስ የተገነባውን አዳሪ ትምህርት ቤት መመረቅ ይሆኗል።
የትምህርት ቤቱን ግንባታ መርቀው ስራ ያስጀመሩት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልእክታቸው፤ በክልሉ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት የተማረ ትውልድ ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በ138 ሚሊየን ብር የተገነባው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ስራ መጀመሩ ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
👉የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት
የበረራ ቅኝታችን ቀጥሎ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቂምቢቢት ወረዳ በመስኖ እየለማ ያለ የስንዴ ምርት የመጎብኘት እድል አግኝተናል።
በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ቂምቢቢት ወረዳ በ21 ሺህ 463 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የመስኖ ስንዴ ሰብል መሰብሰብ ተጀምሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ፤ በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የበጋ መስኖ ልማት ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የአርሶ አደሩን ገቢ እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
የበጋ መስኖ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።
የግብርና ሜካናይዜሽንን በስፋት በመጠቀም እንዲሁም ፈጠራን በማከል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረቱ በተሳካ መልኩ መቀጠሉን አንስተዋል።
👉ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ዓለም አቀፍ ክስተት ነው። ችግሩ በተለይም በታዳጊ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ ጉዳቶችን እያስከተለ ይገኛል።
ኢትዮጵያም የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደመሆኗ መጠን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መፍትሄ ለመስጠት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።
በዚህ ረገድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና ፍልሰትን ለመግታት በሚከናወኑ ሥራዎች በምርምር እያገዙ ናቸው።
በሂደቱ ውጤታማነት ላይ የሚመክር መድረክ በሰመራ በተደረገበት ወቅት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲዎች የሕግና ማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኖች ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት በምርምርና በማማከር እያገዙ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሰዎች ህገወጥ ዝውውርንና ፍልሰትን ለመግታት የነፃ የሕግ ድጋፍና የማማከር አገልግሎትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ለህብረተሰቡ እየሰጡ ናቸው።
👉የኢትዮጵያ እያመረተች ነው
በአማራ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር «ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት» በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።
መርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እና ሌሎችም በተገኙበት ተካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የገቢ ምርቶችን ከመተካት ባለፈ ለውጭ ምንዛሬ አይነተኛ የገቢ ምንጭ መሆን አስችሏል ብለዋል።
👉መሶብ በአርባ ምንጭ፣ ዲላ እና ነቀምቴ
በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች እየተስፋፋ የመጣው የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት በዚህ ሳምንት አርባ ምንጭ፣ እና ዲላ ከተሞች ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል።
የመሶብ ማእከላቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀዋል።
የዲጅታል አሰራርን በማስፋት ለዜጎች ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት የመስጠት ጥረቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
👉ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች
በኢፌዴሪ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ መሠረት፣ በመጠለያ የሚገኙ ዜጎች እና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር በተለያዩ ግንባሮችና ካምፖች የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በመደበኛው የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ለመስጠት የሚቸገሩ ስለመሆኑ ያነሳል።
በመሆኑም ይህን መሠረታዊ መብት ለማስከበርና የምርጫውን አካታችነት ለማረጋገጥ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ልዩ መመሪያዎችን በማውጣት ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን አደራጅቷል።
በመሆኑም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በእለቱ ድምፅ መስጠት ካልቻሉት መካከል የሰሜን ምስራቅ ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከቀናት በፊት ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ በአፋር ክልል እና በደብረ ብርሃን ከተማ በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ዜጎች በልዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
👉የመኸር እርሻ ንቅናቄ
በሲዳማ ክልል የመኸር እርሻን በንቅናቄ በመምራት የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡና ገበያን የሚያረጋጉ የግብርና ልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ርእሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት መሬት ጦሙን እንዳያድርና ግብአትን በወቅቱ በማቅረብ እንዲሁም ለግብርና ቴክኖሎጂ ትኩረት በመስጠት ምርታማነቱን ማሳካት አስችሏል።
ዘንድሮም ተግባሩን በማስቀጠል የበልግ ሰብልን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን የመኸር እርሻን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱ በዘገባው ተመላክቷል።
ይህም የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ በማምረት ገበያን ለማረጋጋትና ለኢንደስትሪዎች ግብአት ለማቅረብ ያስችላል ነው የተባለው።
በምርት ዘመኑ የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም አመራሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለውጤቱ መትጋት እንዳለበትም በውይይቱ ተነስቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር ብዜትን በዓይነት፣ በመጠንና በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ተችሏል።
ቢሮው በግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ እና በክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የዘር ብዜት ዕቅድ አፈጻጸምና ዝግጅት ላይ ያተኮረ የባለ ድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግዳልቅ አልቅሚ እንደገለጹት፤ በክልሉ የምርጥ ዘርን በጥራትና በመጠን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ በማድረስ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።
ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓትን ለማቅረብና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር አግዟል።
ተግባሩን በማስቀጠልም በ2017/18 የምርት ዘመን በክልሉ ከ2 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ማምረት መቻሉንም ገልጸዋል።