ቀጥታ፡

የ35ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐ ግብር

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 35ኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎችን ዛሬ ይካሄዳሉ።

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ነገሌ አርሲ ከሃዋሳ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ነገሌ አርሲ በ53 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ሃዋሳ ከተማ በ48 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ከድ የራቀው ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

በ34ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 የረታው ሃዋሳ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ በማለም ወደ ሜዳ ይገባል።

ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ሀዲያ ሆሳዕና ከፋሲል ከነማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና በ43 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ሲይዝ ፋሲል ከነማ በ46 ነጥብ 10ኛ ደረጃ  ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አቻ የወጣው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይፋለማል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን ሶስት ለማግኘት ይጫወታል።

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

አዳማ ከተማ በ39 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ45 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ካለፉት አምስት ሊግ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ያሸነፈው አዳማ ከተማ ከወራጅ ቀጠና ስፍራ ፈቀቅ ለማለት ሶስት ነጥብ ማግኘት ግድ ይለዋል።

በ34ኛ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 ያሸነፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ድሉን ለማስመመዝገብ ይጫወታል።

አርባምንጭ ከተማ ከምድረ ገነት ሽሬ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አርባምንጭ ከተማ በ32 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።  ምድረ ገነት ሽሬ በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

በ34ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማ መቻልን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ተጋጣሚው ምድረ ገነት ሽሬ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

ጨዋታው በወራጅ ቀጠና ለሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች እጅጉን ወሳኝ የሚባል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም