ቀጥታ፡

በዓለም ዋንጫው ጀርመን በመጀመሪያ ጨዋታዋ ድል ቀንቷታል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ አምስት የመጀመሪያ መርሐ ግብር ጀርመን ኩራሳኦን 7 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።

ማምሻውን በሂውስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካይ ሃቫርትዝ (ሁለት ጎሎች)፣ ፍሊክስ ንሜቻ፣ ኒኮ ሽሎተርቤክ፣  ጀማል ሙሲያላ፣ ናትናኤል ብራውን እና ዴኒዝ ኡንዳቭ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሊቫኖ ኮሜኔንሲያ የኩራሳኦ ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ኮሜኔንሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ለተሳተፈችው ኩራሳኦ ግብ በማስቆጠር ታሪክ ሰርቷል።

በጨዋታው ጀርመን ፍጹም የበላይነት ነበራት።

ጨዋታው በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ የግብ መጠን የተቆጠረበት ነው።

ውጤቱን ተከትሎ የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን በሶስት ነጥብ ምድብ አምስትን መምራት ጀምራለች።

ኩራሳኦ ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

በዚሁ ምድብ ኮትዲቭዋር ከኢኳዶር ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም