የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ትብብር ይበልጥ ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ትብብር ይበልጥ ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና የደህንነት ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) ገለጹ።
ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቅድሚያ የሚሰጠው የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው።
ጥያቄው በሁሉም መመዘኛ ተገቢ ነው ያሉት አማካሪው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ለማንሳት ጠንካራ የታሪክ እና የሕግ መሰረት እንዳላት አመልክተዋል።
ይህ የባህር በር የማግኘት እንቅስቃሴ ብሔራዊ ጥቅምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኗል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በሰፊው የማስገንዘብ ሥራ ማከናወኗን ገልጸዋል።
በዚህም ጥያቄው በዓለም አቀፍ መድረክም ከጊዜ ወደ ጊዜ እውቅና እያገኘ መምጣቱን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ ትስስርን እና መረጋጋትን በመምራት ረገድ ታሪካዊ ሚና ያላት ሀገር መሆኑን የገለጹት ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
የቀጣናው ሀገራት ትስስርን በማጠናከር ረገድም የኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠላም ለጎረቤት ሀገራት ሰላም እውን መሆን ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፤ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታ መሠረታዊ በሆነ መልኩ በማረጋጋት ቀጣናዊ ብልፅግና እውን እንዲሆን አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።