ከጤና ጠንቅነት ወደ ንጹህ ውብ መዝናኛ ስፍራነት የተለወጠው የወንዝ ዳርቻ ልማት - ኢዜአ አማርኛ
ከጤና ጠንቅነት ወደ ንጹህ ውብ መዝናኛ ስፍራነት የተለወጠው የወንዝ ዳርቻ ልማት
ከእንጦጦ እስከ ፒያሳ የተዘረጋው የወንዝ ዳርቻ ልማት ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያና ለጤና ጠንቅ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ አረንጓዴ፣ የንግድና የመዝናኛ ማዕከልነት በመቀየር የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ስኬታማ ሥራ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ከእንጦጦ እስከ ፒያሳ (ቀጨኔ መድኃኔዓለም) የተዘረጋው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ የአዲስ አበባን ገጽታ ከመቀየርና የነዋሪዎቿን የኑሮ ጥራት ከማሻሻል አንጻር እጅግ ሰፊና ዘርፈ-ብዙ ትርጉም ያለው ግዙፍ ስራ ነው።
ቀደም ሲል እነዚህ የወንዝ ዳርቻዎች የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ መጣያ፣ እንዲሁም ለከባድ ጠረንና ለበሽታ መፈልፈያነት የተጋለጡ ነበሩ።
ይህ ፕሮጀክት ግን የወንዝ ዳርቻዎቹን በማጽዳትና የተፈጥሮ ፍሰታቸውን ጠብቀው እንዲፈሱ በማድረግ የስነ-ምህዳር መዛባትን ታድጓል።
ፕሮጀክቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አረንጓዴ ተክሎች፣ አበቦችና ዛፎች በመተከላቸው አካባቢው ንጹህ አየር እንዲኖረውና የሙቀት መጠንን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የእግር ጉዞ መስመሮች እና የብስክሌት መንገዶች ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ምቹ ዕድል ፈጥረዋል።
ቤተሰቦችና ጓደኛማቾች የሚገናኙባቸው፣ የተለያዩ ማህበራዊና ባህላዊ ሁነቶች የሚስተናገዱባቸው ሰፊና ውብ ስፍራዎች ተፈጥረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ልማቱ ከመጀመሩ በፊት የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በማስታወስ አሁን የመጣውን ለውጥ አስደሳችና የሚስደንቅ መሆኑን ይናገራሉ።
ወይዘሮ አስናቀች ካሳ እንደገለጹት ፤ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ከመሰራቱ በፊት አካባቢው ንጽህናው የተበላሸ፣ የቆሻሻ መከማቻ እና ለጤና የማይበጅ ነበር።
አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ እጅግ መልካም ገጽታን መላበሱን ልማቱ የአካባቢውን ንጽህና ከመጠበቅ ባለፈ፣ ለልጆች መጫወቻነት፣ ለአዋቂዎች መዝናኛነት እና ለሥራ ዕድል መፍጠሪያነት እየዋለ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ኪዳነቃል እርጌ በበኩላቸው፤ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ለአካባቢው ሰላምና ጸጥታ መከበር ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በልማቱ አማካኝነት በርካታ መንገዶች በመገንባታቸው ለነዋሪዎች ምቹና አማራጭ የትራንስፖርት ዕድል መፍጠሩን አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ የያዛቸው ዘርፈ-ብዙ መሰረተ-ልማቶች ሕፃናትን፣ ወጣቶችንና ወላጆችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሁም ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ያካተቱ ሆነው መገንባታቸው ልዩ ያደርገዋል ስትል የተናገረችው ወጣት አዳነች አይሳ ናት።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ኃይሌ ሰለሞን ከልማቱ በፊት በአካባቢው የወንዝ መሻገሪያ ድልድይ ባለመኖሩ እና በቆሻሻ ሽታ ሳቢያ በእጅጉ ይችገሩ እንደነበር ተናግረው ፤አሁን ግን የአካባቢው ገጽታ ተስተካክሎ ለሌሎች ሰዎች ጭምር ተመራጭ መዝናኛ ሆኖ በመገኘቱ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ሲሉ ገልጸዋል።