አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቅ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማፋጠን እየተሰራ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቅ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማፋጠን እየተሰራ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2018 (ኢዜአ)፦ የምርምር እና አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቅ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማፋጠን እየተሰራ እንደሚገኝ የፌደራል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከሰኔ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ የቆየውን የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር የመዝጊያና የአሸናፊዎች ሽልማት መርሀግብር አካሂዷል።
በመርሀግብሩ የኢፌዲሪ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ጉባኤው አዳዲስ አሰራሮችንና ፈጠራዎችን በማስተዋወቅ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለመደገፍ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
በጉባኤው የቀረቡት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለፖሊሲና ስትራቴጂ ግብዓት የሚሆኑ ሲሆን፣ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማቀላጠፍ በኩል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ10 በላይ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ የምርምርና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በሶስት ቀናት ቆይታ 18 የምርምር ስራዎች፣ 100 የፈጠራ ስራዎችና 34 የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ መቅረባቸው ተናግረዋል።
ከቀረቡት የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መካከል 6ቱ የመጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ከኢትዮጵያ የቀረቡት (IOT SMART IRRIGATION FOR CLIMATE) እና (CEREBRO-LOGIC) አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን፣ ከናይጄሪያ የቀረበው (ECOLYFT) ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ለሽልማት በቅተዋል።
አሸናፊ የሆኑት እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በተግባር ላይ ውለው ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩ ተቋማዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ተገልጿል።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሃብታሙ ሙለጌታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት ሶስት ቀናት በርካታ የምርምር የሳይንስና ቴክኒሎጂ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
እንደ ሀገር በተለይም ከአምስቱ የልማት ምሰሶዎች ትኩረት ያደረጉ ጥናቶች መቅረባቸው ገልፀጸው፤ ጥናቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ የተጀመረው የልምምድ ስራ ሊያዳብሩ የሚችሉ በርካታ የፈጠራ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን የተኪ ምርት ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ከቀረቡት የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መካከል 6ቱ የመጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ከኢትዮጵያ ውስጥ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ሲሆን ከናይጄሪያ የመጣችው ተወዳዳሪ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች።
አንደኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ከዜድ ቴን ቴክኖሎጂ ዘላለም እንዳለው ውድድሩ ጠንካራ እንደነበር ገልጾ፤ አንደኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቁ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል።
የሰራው የፈጠራ ስራ ዘመናዊ የመስኖ መቆጣጠርያና መከታተያ ቴክኖሎጂ ሲሆን 50 በመቶ ውሃን መቆጠብ እንዲሁም 30 በመቶ ምርትን ማሳደግ የሚያስችል እንደሆነ ገልጿል።
አንጎል ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ያለቀዶ ጥገና ህክምና ማወቅ የሚያስችል የፈጠራ ስራ በማቅረብ ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁትን በመወከል የገለጸችው ደግሞ ተማሪ ሩት ተሾመ ናት።