ቀጥታ፡

የደም ልገሳን ባህል በማድረግና የዓይን ብሌንን በመለገስ ለሌሎች ተስፋና ብርሃን የመሆን በጎ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 7 /2018 (ኢዜአ)፦የደም ልገሳን ባህል በማድረግና የዓይን ብሌንን በመለገስ ለሌሎች ተስፋና ብርሃን የመሆን በጎ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አሳሰቡ።


 

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት "ሰብዓዊ ተግባር ህይወትን ይታደጋል፤ ብርሃን ይመልሳል" በሚል መሪ ሀሳብ 23ኛውን የዓለም ደም እና የዓይን ብሌን ለጋሾች ቀንን አክብሯል፡፡

በመርሃ ግብሩም ለደም ለጋሾች እና ለዓይን ብሌን ለጋሽ ቤተሰቦች እንዲሁም በበጎ ተግባሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት ምስጋና እና እውቅና ተሰጥቷል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው፣ የጤና ሚኒስቴር ተቋማት አመራሮች የደም ለጋሾችና የዓይን ብሌን ለጋሽ ቤተሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጎ ፈቃደኝነትና ሰብዓዊነት እንዲጎለብት ትልቅ ምዕራፍ ከፍተዋል።

የደምና ዓይን ብሌን ልገሳ ህይወትን የሚታደግና ብርሃንን ለሰዎች የሚሰጥበት ታላቅ ስጦታ ነው ብለዋል።

ደም በመለገስ ህይወት እናስቀጥላለን፣ ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌን በመለገስ ለዜጎች ብርሃን እንሰጣለን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ፤ ለዚህም ከኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ጋር በመተባበር ይህን ስራ ለማስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ደም የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ፣ በቀዶ ህክምና፣ በትራፊክ አደጋ እንዲሁም በካንሰርና ኩላሊት ህመም እንዲሁም በሌላ ህመም ደም ለሚሹ ወገኖች ለመድረስ የሚያስችል ውድ ስጦታ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ የደም አቅርቦት ለጤና ተቋማት በዘላቂነት ተደራሽ ለማድረግ ከአገልግሎቱ ጋር በመሆን ከ60 በላይ ደም ባንክ እንዲቋቋም ማድረጉንም ገልፀዋል።

አገልግሎቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍ የመመርመሪያ ኪቶችን ከማሰራጨት ባለፈ ዘመናዊ የዲጂታል የደም መረጃ ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ሲሆን የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጅማ ከተማ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የደም ልገሳን ባህል ለማድረግና የዓይን ብሌን ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ ህብረተሰቡም በዚህ በጎ ተግባር ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው፥ አንዲት ከረጢት ደም የሰው ህይወት ትታደጋለች የዓይን ብሌንም ብርሃን ትለግሳለች ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት 11 ወራት ከ400 ሺህ በላይ ከረጢት ደም መሰብሰቡንና ይህም የደም ልገሳ ባህል እየተሻሻለ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልፀዋል።

እያንዳንዱ የደም ዩኒት ስጦታ የፍቅርና የደግነት ተግባር ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የጤና ፖሊሲና ሥርዓት አማካሪ ዶክተር ቢጆይ ናምቢያር ናቸው። 


 

ደም መለገስ ለታካሚዎችና ለቤተሰቦቻቸው ተስፋን የሚሰጥ ትልቅ ስጦታ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የደም ልገሳን ባህል ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር፣የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎትና ለጋሾች እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ የሚበረታታ መሆኑንና የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ረገድ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም