በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ለትውልድ የሚሸጋገር ስትራቴጂክ የዲፕሎማሲ አጋርነት እየጎለበተ ነው-አምባሳደር ጀማል በከር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ለትውልድ የሚሸጋገር ስትራቴጂክ የዲፕሎማሲ አጋርነት እየጎለበተ ነው-አምባሳደር ጀማል በከር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ለትውልድ የሚሸጋገር ተምሳሌታዊ ስትራቴጂክ የዲፕሎማሲ አጋርነት እየጎለበተ መሆኑን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ ያካሄደችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገሪቷን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ ሁለንተናዊና ስትራቴጂካዊ ጥምረት የገነቡ ሀገራት ናቸው፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገነቡት ስትራቴጂካዊ ጥምረት በታዳሽ ኃይል እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ በላቀ ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቷል።
በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከኢዜአ የውጭ ቋንቋ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሰፊና ጥልቅ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን እያካሄደች ትገኛለች ብለዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር አርዓያነት ያለው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር መፍጠር እንድትችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ብቻ ሳይሆን፣ አዳዲስ ዕድሎችን ለሚፈልጉ ለሌሎች ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማትም ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምሥራቅና ለተቀረው ዓለም ያላት ስትራቴጂክ መገኛነቷ በሁሉንም ረገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ንጹሕና ለአካባቢ ተስማሚ አረንጓዴ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ጠቁመው፤ መንግሥት አልሚዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ያለው ዝግጁነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በዚህም ሀገሪቱ የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ እየተስፋፋ በመሆኑ የንግድ ሥራን ለማቀላጠፍና የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማጠናከር ረገድ ትልቅ እመርታ ማሳየቷንም አክለዋል።
አምባሳደር ጀማል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጨምሮ ሌሎች የውጭ ሀገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ማለትም በግብርና እና ግብርና ማቀነባበሪያ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በቱሪዝም፣ በአገልግሎት፣ በከተማ ልማት እና በሪል ስቴት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩም አበረታተዋል።