ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ስፖርታዊ ውድድሮችን የማስፋትና ዘርፉን በእውቀት የመምራት ጥረቶች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ስፖርታዊ ውድድሮችን የማስፋትና ዘርፉን በእውቀት የመምራት ጥረቶች ይጠናከራሉ
ባህር ዳር፤ ሰኔ 7/2018 (ኢዜአ)፦ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ስፖርታዊ ውድድሮችን የማስፋትና ዘርፉን በእውቀት የመምራት ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን ገለጸ።
1ኛው የኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር፣ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
በወቅቱም ኮማንደር ስለሺ ስህን እንደገለጸው፤ በኢትዮጵያ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት የአትሌቲክስ ስፖርቱን በእውቀትና በአሰራር ማዕቀፍ ለማዘመን እየተሰራ ነው።
የአትሌቲክስ ውድድሮችን በማዘጋጀት ተተኪ አትሌቶችን ለመመልመልና ታዋቂ አትሌቶች ደግሞ አቋማቸውን እንዲፈትሹ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችን በዘላቂነት በማጠናከር ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያላትን የበላይነት ማስቀጠል ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚሳተፉ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ከ120 በላይ ወንድና ሴት አትሌቶች የተሳተፉበትና 10 ኪሎ ሜትርን የሸፈነ ውድድር መካሄዱን ጠቁመዋል።
በቀጣይ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርን በማስፋት በርካታ የአትሌቲክስ ክለቦች እንዲያሳተፉ እንደሚደረግም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ባህል፣ ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ጸጋዬ በበኩላቸው፥ ባህር ዳርን ጨምሮ በክልሉ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ የኮሪደርና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለሩጫ ውድድሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
የባህርዳር ከተማ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የሚመረቀውን የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ገንብታ ለስፖርት ዘርፉ ዕድገት እየሰራች መሆኗን ጠቁመው የኮሪደር ልማቷም ለዛሬው ሩጫ ውድድር የተመቸ ድባብን ፈጥሯል ብለዋል።
ይህንን ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማት በመጠቀምም ክልሉን በስፖርት ኢንቨስትመንት ተመራጭና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የ10 ኪ/ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቀቀው የአማራ ማረሚያ ቤቶች አትሌት ጀማል ይመር እንደገለጸው፣ ውድድሩ ለብቃት መለኪያና ለተተኪዎች ትልቅ መድረክ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል።
ሌሎች ተመሳሳይ ውድድሮችን በሌሎች ክልሎች በሚገኙ ከተሞች በማዘጋጀትና የውድድር መድረክ በመፍጠር የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባም አመልክቷል።
ውድድሩ ስፖርታዊ አቋሟን ለመፈተሽ እንዳገዛት የገለጸችው ደግሞ በሴቶች 1ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ ሯጯ አትሌት ውዴ ከፍያለው ናት።
በመርሃ ግብሩ ላይም የፌዴራልና የክልል የዘርፉ አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ ለአሸናፊ አትሌቶችም የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።