ቀጥታ፡

በከተማችን የተከናወኑ የሰላምና ልማት ተግባራት ውጤታማና ልምድ የሚወሰድባቸው ናቸው- የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች

ወልድያ ፤ሰኔ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በከተማችን የተከናወኑ የሰላምና ልማት ተግባራት ውጤታማና ልምድ የሚወሰድባቸው ናቸው ሲሉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ነዋሪዎቹ እንደገለፁት፤ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን ተሰልፈን የከተማችንን ሰላም በንቃት በመጠበቅ የተጀመሩ አስደናቂ የልማት ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን።

ነዋሪዎቹ አክለውም በከተማችን የተከናወኑ የሰላምና ልማት ተግባራት ውጤታማና ልምድ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል።

ከነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ያልጋ ጌታሁን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማው እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው።

በከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የአስፋልት መንገድ፣ የሳይንስና የፈጠራ ማዕከል፣ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍትና የሥራ እድል መፍጠሪያ ሼዶች እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል።

እየተገነቡ የሚገኙት የልማት ስራዎችም የከተማውን ውበትና ገጽታ ከማሳመር ባለፈ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ''ወልዲያ ሰላም እንዳልሆነችና በችግር ውስጥ የምንኖር ለሚመስላቸውም አካላት በከፍተኛ የልማት ጉዞ ላይ መሆናችን በተግባር በማሳየት ምላሽ የሰጠ ነው'' ያሉ ሲሆን በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ልማቱን በማስቀጠልም ልጆቻችን የስራ እድል እንዲያገኙ፣ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃና ከተማችን የቱሪስትና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ከመንግስት ጎን ተሰልፈን እንሰራለን ብለዋል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ተጓዳ ፍቅሩ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በሌሎች ከተሞች የተከናወነው የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች አሁን በከተማዋ ተተግብሮ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

ይህም የከተማ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ለልማት ስራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ የመጣ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

"እኛም ከመንግስታችን ጎን ተሰልፈን የልማት አርበኛና የሰላም ዘብ በመሆን በዘላቂነት ለመስራት ቆርጠን ተነስተናል" ብለዋል።

አቶ ቸርነት እሸቴ በበኩላቸው የኮሪደር ልማት፣ የመንገድ፣ የወጣቶች መዝናኛ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትና ሌሎችም በፍጥነትና በጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ከተማዋ በፈጣን ልማትና ዕድገት ላይ ለመሆኗ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ከተማዋ መማሪያና ልምድ የሚወሰድባት በመሆኗ ተደስተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም