ቀጥታ፡

በዓለም ዋንጫው ኮትዲቯር ከኢኳዶር ቱኒዚያ ከስዊድን የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7 /2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ አምስት መርሐ ግብር ኮትዲቯር ከኢኳዶር ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ታከናውናለች።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኮትዲቯር በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ተጋጣሚዋ ኢኳዶር ለአምስተኛ ጊዜ በውድድሩ ላይ ተሳትፎ ታደርጋለች።

የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ባደረገቻቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዳለች። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይታለች።

በተሳትፎዋ ታሪክ ከምድቧ አልፋ አታውቅም።

ኢኳዶር በዓለም ዋንጫው እስከ አሁን 13 ጨዋታዎችን አከናውና በአምስቱ ድል ሲቀናት በስድስት ጨዋታዎች ሽንፈትን ቀምሳለች።

በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥታለች።

ኢኳዶር እ.አ.አ በ2006 በጀርመን በተካሄደው 18ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ደርሶ በእንግሊዝ 1 ለ 0 የተሸነፈችበት አጋጣሚ በውድድሩ ላይ ያስመዘገበችው ትልቁ ውጤቷ ነው።

ኮትዲቯር እና ኢኳዶር የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚሁ ምድብ አምስት ጀርመን ከኩራሳኦ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በሂውስተን ስታዲየም ይጫወታሉ።

የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ እና ለ21ኛ ጊዜ በውድድሩ ላይ የምትሳተፈው ጀርመን ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ግምት አግኝታለች።

156 ሺህ ህዝብ ገደማ ያላት የደሴቲቷ ሀገር ኩራሳኦ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የምታደርገው ተሳትፎ ትኩረት የሳበ ሲሆን ዜጎቿም ጨዋታውን በጉጉት ይጠብቁታል።

በተያያዘም በዓለም ዋንጫ በምድብ ስድስት ቱኒዚያ ከስዊድን ጋር ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ በሞንትሬይ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ በወዳጅነት ጨዋታዎች ተገናኝተው ስዊድን ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ ቱኒዚያ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ቱኒዚያ በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በነበራት ተሳትፎዎቿ ከምድቧ አልፋ አታውቅም።

ስዊድን ለ14ኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ላይ ትሳተፋለች።

ትልቋ ውጤቷ ራሷ እ.አ.አ በ1958 ባዘጋጀችው ስድስተኛው የዓለም ዋንጫ በፍጻሜው በብራዚል 5 ለ 2 ተሸንፋ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው።

በምድብ ስድስት ሌላኛው መርሐ ግብር ኔዘርላንድስ ከጃፓን ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በዳላስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም