ቀጥታ፡

በዞኑ የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ ለኑሮ ተስማሚ እና ለጤና ምቹ አካባቢዎችን እየፈጠረ ነው

ወልቂጤ ፤ ሰኔ 7/2018(ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን "ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ  ለኑሮ ተስማሚ እና ለጤና ምቹ አካባቢዎችን እየፈጠረልን ነው ሲሉ  የዞኑ  ነዋሪዎች ገለጹ።

በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ ኸምብያቴ ቀበሌ የፅዱ መንደር እውቅና የተሰጠ ሲሆን የፅዱ ኢትዮጵያ መስፈርትን ያሟሉ አካባቢዎች እና ግለሰቦች ቤት  ምልከታ ተደርጓል ።

የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ በሀገሪቱ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ለማሻሻል፣ የገጠርና የከተሞችን ውበት ለመጠበቅ እና ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር ያለመ ሀገራዊ ዘመቻ ነው። 


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው ኢንሼቲቭ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ የኸምብያቴ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዓመቱ ብዙ የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ መተግበር የውሀ ብክለትን በመከላከል፣ የፅዳት ዘመቻና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስራዎችን ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር እንዳስቻላቸው ጠቅሰዋል።


 

ደጃቸው፣ ቤታቸውንና ጓሮአቸው ፅዱ እና ውብ ማድረጋቸውን ጠቁመው ይህም በጤናቸው እና በኑሮቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው አቶ ገብሬ ዛጋ የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ የተሻለ መፀዳጃ ቤት እንዲጠቀሙ በማድረጉ ከንፅህና ጉድለት የሚመጣ በሽታን ለመከላከል እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።


 

የተፈጠረውን ግንዛቤ እና ስልጠና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚተገብሩት ተናግረዋል።

የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ የአካባቢ ጽዳትና ውበትን በጋራ በመጠበቅና በመንከባከብ ምቹና ተመራጭ አኗኗርን ፈጥሮልናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ክብነሽ ፉጃጋ ናቸው ።


 

አካባቢያችንን ፅዱ እና ለመኖሪያ ምቹ በማድረግ ረገድ እንዲሁም ተስማሚ መንደርን በመፍጠር በኩል በቅንጅት መስራታችን ለውጤት አብቅቶናል ብለዋል።

የጌታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በህሩ ኸይረዲን የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ ከብክለት የፀዳ ወረዳን እውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠሩን አንስተዋል።

ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተሰራው ስራ የእናቶች ወሊድ ክትትልና አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በህክምና ተቋማት ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።

በወረዳው የሚገኙ የጤና፣ የትምህርት፣ የእምነት እና ሌሎችም ተቋማት ጭምር ፅዱና ምቹ እየተደረጉ መሆናቸውን አንስተው እውቅና ለተሰጣቸው ፅዱ ቀበሌዎች ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።


 

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ በዞኑ ህዝብ ጤና እና አኗኗር ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲተገበር አድርጎታል ብለዋል።

እስካሁን በዞኑ ከሚገኙ 315 ቀበሌዎች መካከል 87 በመቶ ያህሉ የዚህ ኢንሼቲቭ ትግበራ ተጠቃሚዎች መሆን መቻላቸውንም ለአብነት አስረድተዋል። 

መርሃ ግብሩ የተሻሻሉ መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት የሰውና የእንስሳት መኖሪያን በመለየት ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እያስቻለ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም