ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማት ስኬት ታዳጊዎች ስፖርታዊ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት መሰረት ጥሏል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማት ስኬት ታዳጊዎች ስፖርታዊ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት መሰረት መጣሉን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

በመዲናዋ የተገነቡ ማራኪ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ አስችሏል።

የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶቹም የመዲናዋን ወጣቶች ስብዕና በመገንባት ስፖርታዊ ክህሎታቸውን የሚያበለፅጉበትን አስቻይ ምኅዳር ፈጥሯል።

ይህም የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማት እጥረትን በመቅረፍ በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ብቃት ያላቸው ወጣት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ መደላድል እየፈጠረ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመዲናዋ የልማት ስኬቶች ለስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ምቹ መደላድልን መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

አዲስ አበባን የማስዋብ የልማት ውጤቶችም ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ውጤታማ የስፖርት ማዕከላትና ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲገነቡ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ብቃትና ጥራት ያላቸው ታዳጊ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ 2 ሺህ 581 የስፖርት ማዘውተሪያና ማሰልጠኛ ማዕከላት መገንባታቸውን አስታውቀዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፋራና ማዕከላት ግንባታም በትምህርት ቤቶች፣ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛና ጤና ተቋማት ጨምሮም በመኖሪያ መንደሮች ላይ አካታች የስፖርት መሰረተ ልማት  ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን አስረድተዋል።  

የመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያና ማሰልጠኛ ማዕከላቱም ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያስገኙ መሆኑን አንስተዋል።

በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ዜጋን በማፍራትም ወጣቶችና ታዳጊዎች ጊዜያቸውን ከአልባሌ ስፍራ ማራቅ ያስቻለ ምኅዳር መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያዎችም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የምታስተናግድበት አቅም የፈጠሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በስፖርት ማዘውተሪያና ማሰልጠኛ ማዕከላት የሰለጠኑ ታዳጊዎች ወደተለያዩ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ የስፖርት ደረጃ እየተሸጋገሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም በኢትዮጵያ የስፖርት ልማት ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ በማበርከት ታዳጊዎች ስፖርታዊ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት መሰረት መጣሉን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

በቀጣይም ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ የስፖርት ማዘውተሪያና ማሰልጠኛ ማዕከላት የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም