የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሀገርን ስም የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሀገርን ስም የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሀገርን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ እውቅ አትሌቶችንና ስፖርተኞችን የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የስፖርት ክለብ እንዲሁም የሙዚቃና ቴአትር ቡድን የተመሠረቱበትን 40ኛ ዓመት በዓል ባከበሩበት መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ለታዋቂዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ የተሰጠ ሲሆን፤ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በስፖርት ክለቡና በኪነ-ጥበብ ቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።
የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የኮሚሽኑ የስፖርት ክለብ ባለፉት 40 ዓመታት በሀገሪቱ የስፖርት ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ማሳረፉን ገልጸዋል።
የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ያደረጉ እውቅ አትሌቶችንና ስፖርተኞችን በማፍራት በኩል ተቋሙ የተጫወተው ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ በስፖርትና በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የጀመራቸውን አበረታች ሥራዎች ይበልጥ ዘመናዊ በማድረግ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ የሚላኩ ታራሚዎችን አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጋ አድርጎ የማውጣት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት የስፖርት ክለቡ እንዲሁም የሙዚቃና ቴአትር ቡድኑ የሕግ ማረም ሥራውን በጥበብና በማስረጽ፣ እንዲሁም በስፖርት የአካል ብቃት በማጎልበት ታራሚውን እያዝናኑና እያስተማሩ በመቅረጽ በኩል ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል።
ሁለቱም ክፍሎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም የስፖርት ክለቡ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረኮች የሀገርን ስም ያስጠሩ በርካታ ጀግና ስፖርተኞችን ያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአትሌቲክሱ ዘርፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊትና ጥቁር ሴት የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነችውን ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን፣ ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን፣ አትሌት ስለሺ ስህን እንዲሁም የማራቶን ጀግናዋን ፋጡማ ሮባን ማፍራቱን በኩራት አስታውሰዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የሙዚቃና ቴአትር ቡድኑ በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ደማቅ አሻራ ያሳረፉና ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በርካታ የጥበብ ባለሙያዎችን ለሀገር ማበርከቱን ጠቁመዋል።