ቀጥታ፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ነው -አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 6 /2018 (ኢዜአ) ፦ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጡበት መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተሳተፉና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት፤ ምክር ቤቱ ምርጫው በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ላዘጋጀው የዕውቅና መርሐ ግብር ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

የተቋም ግንባታ የሥልጣኔ መገለጫ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አደም ፋራህ፤ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው የሕልውና እና የብልፅግና መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዴሞክራሲ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የምንገነባበት ምሰሶ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት አቶ አደም፤ ሀገራዊ ተቋማትን በጋራ ጥረትና መሥዋዕትነት መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በምርጫው ወቅት የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ፅኑ ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳየበት መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በምርጫው ወቅት የነበረውን ንቁ ተሳትፎ አድንቀው፤ በተለይም ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ድርጅቶቹ ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የሲቪክ ማኅበራት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ሚና እንዲያሳድጉ ሰፊ ሥራ መሠራቱን የጠቀሱት አቶ አደም፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የታየው ከፍተኛ ተሳትፎም ያለፈው ጥረታችን ውጤት ነው ብለዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ይበልጥ ለማጠናከርና አጋርነታቸውን ለማስቀጠል መንግሥት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በፖለቲካው ምኅዳር በፉክክርና በትብብር መካከል ያለውን ሚዛን ጠብቆ የመሄድ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም