ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፀረ-ዶፒንግ ትምህርት ጉባኤ ለማዘጋጀት ተመረጠች

  አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ዶፒንግ ትምህርትና ስልጠና ጉባኤ (Global Education Conference) እንድታስተናግድ መመረጧን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ለስፖርት ልማት በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ዓለም አቀፍ የስፖርት ኩነቶች ለማዘጋጀት ጥረት እያደረገች ትገኛለች። 

እ.ኤ.አ በ2027 የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ዶፒንግ ትምህርትና ስልጠና ጉባኤ (Global Education Conference) እንድታስተናግድ መመረጧን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

በዓለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) አዘጋጅነት በየጊዜው በመካሄድ ላይ የሚገኘው ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አንድምታ ያለው ሁነት መሆኑ ተገልጿል።

ቀደም ሲል እ.ኤ.አ በ2018 በቻይና ቤጂንግ፣ በ2022 በአውስትራሊያ ሲድኒ እንዲሁም በ2024 በፈረንሳይ ሀገር መካሄዱ ይታወሳል።

ይህ ጉባኤ በአፍሪካ ደረጃ ሲካሄድ የመጀመሪያው በመሆኑ ለኢትዮጵያ የገፅታ ግንባታ እና ለስፖርት ቱሪዝም እድገት ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ በተጨማሪ፣ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴውን የበለጠ በማጎልበትና ንፁህ ስፖርትን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተነግሯል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በመደበኛ የትምህርት ስርዓት ውስጥ አካትቶ መተግበርን፣ በቂ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ተግባራዊ ማድረግን፣ እንዲሁም ጠንካራ የምርመራና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግን ጨምሮ ያስመዘገበቻቸውን በርካታ ውጤቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአግባቡ ለማስገንዘብ ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥር የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም