ቀጥታ፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሥጋት ቀጣና ወጥተው ወደ እውነተኛ የልማት አጋርነት ተሸጋግረዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከቀድሞ የሥጋትና የጥርጣሬ ቀጣና ወጥተው ወደ እውነተኛ የመንግሥት የልማትና የዴሞክራሲ አጋርነት መሸጋገራቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተሳተፉና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

"የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ያመሰግናሉ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ሚኒስትሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሕዝብን ድምፅ የሚያሰሙና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የመተማመን ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መሠረታዊ ዓላማቸው የሕዝብን ድምፅ ማስተጋባትና የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል በነበሩ ሕጎች ምክንያት እንደ ሥጋት ታይተው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በተለይም የአዋጅ ቁጥር 621/2009 መውጣት መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ከአጋዥ ይልቅ እንደ ሥጋት እንዲመለከታቸው አድርጎ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ሆኖም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት ከቁጥጥር ወደ አጋርነት፣ ከገደብ ወደ ትብብር እንዲሸጋገር መደረጉን አብራርተዋል።

በዚህም ማህበራቱ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ መቻላቸውን ገልጸዋል።

በሰብዓዊ መብትና በማኅበራዊ ተጠያቂነት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውን በመጥቀስ፤ ምርጫ የዴሞክራሲ ፅንሰ-ሐሳብ አንድ አካል መሆኑን ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብ ትልቅ ዕድል ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ተመልካች ሳይሆኑ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።

የሲቪል ማኅበራት ስኬት የሚለካው ሰላም፣ ልማትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዲገነባ በማድረግ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገለልተኛ ተቋማዊ ብቃት ኃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቷል ብለዋል።

ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የጸጥታ አካላት የነበራቸው ሚና የጎላ እንደነበር በማንሳት፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አማራጭ ሐሳቦችን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰማራት አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ የምስጋና መርሐ ግብሩ የተዘጋጀላቸው የሕግና የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሁም ሚዲያዎች በሙሉ ትልቅ ክብርና ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም