ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገራችን ያለንን ፍቅርና የሰላም ቀናኢነት በተግባር አስመስክረናል - የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚሊዮኖች በመመዝገብ በፅናት በመምረጥ ለሀገራችን ያለንን ፍቅርና የዘላቂ ሰላም ቀናኢነት በተግባር አስመስክረናል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን የገለጹት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተሳተፉና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ ነው።


 

"የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ያመሰግናሉ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ሚኒስትሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ እስከ ምርጫው ዕለት በኢትዮጵያዊ ስክነት በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያውያን ከራሳችን አልፎ ለዓለም ውህደትና ልማት መሠረት የሆኑ የጥንታዊ ሀገር በቀል እሴቶች ባለቤት ነን ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ይህ የኢትዮጵያ እሴት ግን ተገቢው የፖለቲካ ልምድ ታክሎበት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይሸጋገር እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስገንዝበዋል።

በዚህም በውይይት፣ በንግግርና በሀሳብ ልዕልና ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት በመሞከሩ የዴሞክራሲ ሂደቱ ፈታኝ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ከታሪካዊ ሥልጣኔያችን አኳያ የተመኘነውን ያህል መራመድ ባንችል እንኳ፣ ያለፈውን ስህተት አርመን የተሻለች ሀገር ለመገንባት ቁጭታችንን ስንቅ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያውያን ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ባለው ሂደት ፍትሐዊና ሰላማዊ መንገድ በመከተል፣ ለዘመናዊ መንግሥት ግንባታ ፍትሐዊ ምርጫ ቁልፍ መሆኑን በተግባር አሳይተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ተስፋ የሚለመልመው በሰለጠነ ምርጫ ነው በሚል በሚሊዮኖች በነቂስ ወጥተን በመምረጥ የነውጥ፣ የጥፋትና የሞት ድግስን ማክሰም ችለናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በትዕግሥት ድምፅ በመስጠት የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ በእጃችን መሆኑን በአሻራችን አትመናል ሲሉ ተናግረዋል።


 

ለሕግ የበላይነት መገዛት፣ ውይይትና ንግግር የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በምርጫው ሂደት ለሰለጠነ የሀሳብ የበላይነት ያለንን ዝግጁነት ያሳየንበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ምርጫ በጥቂት ልሂቃን መካከል የሚደረግን ውድድር ለመታዘብ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት የሚደረግ የዴሞክራሲ መንገድ መሆኑን አብራርተዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጎላ አበርክቶ ላደረገው ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለጸጥታ ኃይሎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም