ቀጥታ፡

በክልሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍ ለሁለንተናዊ ልማት ያላቸውን አበርክቶ ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ይጠናከራል

ቡታጅራ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍ ለሁለንተናዊ ልማት ያላቸውን አበርክቶ ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ። 

በክልሉ "ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የሳይንስ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክና አውደ ርዕይ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አንተነህ ፈቃዱ እንደገለጹት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች ለሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ፋይዳቸው የጎላ ነው። 

በክልሉም ግብርናና ኢንዱስትሪን ጨምሮ በሌሎች የልማት መስኮች የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት በኩል ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍ ለሁለንተናዊ ልማት የሚኖራቸውን አበርክቶ ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

በዘርፉ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በትምህርት ተቋማት ላይ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።


 

የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ ሰላሙ አማዶ በበኩላቸው እንዳሉት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር በመፍታት በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።

የፈጠራ ባለቤቶችን በማበረታታትና ተጠቃሚነታቸውን በማሳደግ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ሥራዎችን ለኢንዱስትሪዎች በማሸጋገር ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ያሉት ደግሞ የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሀላፊ ሙስጠፋ ኢሳ ናቸው።

በክልሉ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ከማፍለቅ በተጨማሪ ተኪ ምርት በማምረት በኩል የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመው፣ የዘርፉን ስኬቶች ለማጠናከር ቢሮው አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በምርምር ለከናወነው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እንደተሰጠው የተናገረው ወጣት ተመስገን በቀለ፣ በክልሉ በተደረገለት ድጋፍና ክትትል በእንሰት በሽታ መከላከል የሚያስችል ምርምር ማድረጉን ተናግሯል።

በመድረኩ ማጠቃለያ በቡታጅራ ከተማ በተዘጋጀ  3ኛው ዙር  ክልላዊ የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎች አውደ ርዕይ ለእይታ ከቀረቡ 146 የፈጠራ ሥራዎች ለተሻሉት እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም