ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት መጎልበትና ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ሚና እያበረከተች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት መጎልበትና ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ሚና እያበረከተች ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት መጎልበትና ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ሚና እያበረከተች መሆኗን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የነጻ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት የጤና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የጤና ዘርፍ አገልግሎቶችን፣ የጤና ተቋማትንና የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ባለሙያዎቹ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ካደረጉት ጉብኝት መካከልም የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት (AHRI) አንዱ ነው፡፡
የዚህ የመስክ ጉብኝት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ተጨባጭ ሥራና ያላትን አቅም ለሰልጣኞቹ በተግባር ማሳየት እንደሆነ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት፤ ጤና ድንበር የለውም፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ለሚሆኑ የጎረቤት ሀገራት የጤና ባለሙያዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት እያስተማረች ትገኛለች።
ይህ ዓይነቱ የልምድ ልውውጥና የባለሙያዎቹ ጉብኝት በምሥራቅ አፍሪካና በአጠቃላይ በአህጉሪቱ በጤናው ዘርፍ በጋራ ለመሥራትና የቀጣናውን አቅም በጋራ ለማሳደግ ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምትሰጠው ነፃ የትምህርት ዕድል ቀጣናዊ ግንኙነትን እያጠናከረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ድንበር የለሽ የሕክምና ዲፕሎማሲ ሚናዋን በተግባር እያሳየች ትገኛለች ብለዋል፡፡
በዚህም የአፍሪካ የጤና ሥርዓት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ጠቅሰው፣ በትምህርት ላይ የሚገኙት የውጭ ሀገራት ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ አጋርነትና ቀጣናዊ ሚና ዕውቅና እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው ዶክተር ሶቤክ ጆን በጉብኝቱ መደሰቱን ገልጾ፣ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎችን መመልከት መቻሉን ገልጿል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ዶክተር ሲሃም መሐመድ በበኩሏ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነችው ያለው ሥራ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብላለች።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያከናወነቻቸው ሥራዎች በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ዶክተር ኬጂ ጌርሚሊዮማ ናት።