ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሠራር ይጠናከራል

አዳማ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚጠናከር የክልሉ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ገለጸ።

የትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከክልሉ 21 ዞኖችና ከተሞች የተውጣጡ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ተጠናቋል።


 

የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ዋና ኃላፊ ከማል ማሜ እንደገለጹት፤ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።

የትራንስፖርት አቅርቦቱን ቀልጣፋና የተሳለጠ ከማድረግ ባለፈ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ትኩረት ተድርጎ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍና አሠራሩን ወደ ዲጂታል ሥርዓት የማስገባት ሥራ በትኩረት እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተቆጣጣሪዎችን አቅም መገንባት፣ የፍጥነት ገደብን መቆጣጠር፣ የተሽከርካሪዎችን የቴክኒክ ብቃት መፈተሽና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለስኬታማነቱም ኅብረተሰቡ ስለ ትራፊክ ደህንነት ያለውን ግንዛቤ ከማሳደግ ጀምሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

በኤጀንሲው የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ ሌችሳ ሃዩ በበኩላቸው፤ በዘርፉ የሚስተዋለውን የሥነ-ምግባር ጉድለት ለመቅረፍ በአመለካከትና በአቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ለትራፊክ አደጋ መንስኤ የሆኑትን ሕገ-ወጥ አሠራሮች ለመግታት ከቴክኖሎጂ ጋር ራሱን የገነባና በሥነ-ምግባር የታነጸ የሰው ኃይል በመገንባት ረገድ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የትራፊክ መቆጣጠሪያ ራዳሮችና የአልኮል መጠን ልኬት ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ የማድረግና አጠቃቀማቸውን የማሳደግ ሥራ በስፋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አሳምነው አብዲሳ በበኩላቸው፤ የትራፊክ ፖሊሶችና የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ኃላፊነታቸውን በቅንጅት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በትራፊክ አደጋ ምክንያት እየደረሰ ያለውን የሕይወትና የንብረት ጉዳት ለመግታት፣ ኮሌጁ ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር በአቅም ግንባታ ላይ በስፋት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም