በክልሉ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ባለፈ ለሰው ሀይል እና ለግብአት አቅርቦ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተገነቡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡
ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ከበቁት አዳዲስ ፕሮጀክቶች መካከል የኦክሲጂን ማምረቻ፣ የልዩ ቀዶ ሕክምና እና የጽኑ ሕሙማን ሕክምና ክፍል እንዲሁም የጡት ወተት ባንክ ይገኙበታል።
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በምረቃ መርሀ ግብሩ እንደተናገሩት በክልሉ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም በሀገራዊ የጤና አገልግሎት ሪፎርም መሰረት የጤና ተቋማትን የማስፋፋት፣ የውስጥ ግብአቶችን የማሟላትና የጤና ባለሙያዎችን በበቂ ሁኔታ የመመደብ ሥራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በነባርና አዳዲስ የሕክምና አገልግሎቶቹ ማህበረሰቡን በላቀ ደረጃ ለማገልገል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቶቹ ሰፍተውና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ መንግስት ከሆስፒታሉ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው እንደ ሀገር የተቀመጠው የጤና ፖሊሲ በሽታን መከላከል ብቻ ሳይሆን አክሞ ለማዳንም የላቀ ትኩረት የሰጠ ነው ብለዋል።
በዚህም በእናቶችና ሕፃናት ሞት መቀነስ እንዲሁም በሌሎች የጤና አገልግሎቶች ላይ በተሰሩ ስራዎች ስኬቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
በሆስፒታሉ እውን የተደረገው የጡት ወተት ባንክ በተለይ ጨቅላ ሕፃናትን ለመንከባከብና ከሞት ለመታደግ ቁልፍ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።
የኦክሲጅን እና የሕክምና ጋዝ ማምረቻ ለሆስፒታሉ እና በአጎራባች ለሚገኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት አቅም ያለው ነው ብለዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) ዛሬ ለተመረቁት ፕሮጀክቶች ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና በጀቱም ከፌዴራል መንግስት የተገኘ መሆኑ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ በሲዳማ ክልልና በአጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው የተመረቁት ፕሮጀክቶች ይህን አገልግሎቱን በተሻለ ጥራት መስጠት ያስችሉታል ነው ያሉት።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ፍፁም ወልደገብርኤል በበኩላቸው ሆስፒታሉ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት አሰራሮችን ከማሻሻል ባለፈ አዳዲስ አገልግሎቶችን እያሰፋ መሆኑን ተናግረዋል።