የኦዲት ሥራን ዲጂታላይዝ በማድረግ የኦዲት ውጤት ጥራት እንዲኖረው እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኦዲት ሥራን ዲጂታላይዝ በማድረግ የኦዲት ውጤት ጥራት እንዲኖረው እየተሰራ ነው
አዳማ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የኦዲት ሥራን ዲጂታላይዝ በማድረግ ኦዲተሮች ሥራቸውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያከናውኑና የኦዲት ውጤት ጥራት እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
መሥሪያ ቤቱ ከክልሉ ለተውጣጡ ከ300 በላይ ኦዲተሮችና አመራሮች በአዲሱ የክዋኔ ኦዲት እና የፋይናንሺያል ኦዲት ማንዋል ላይ ያዘጋጀው የአምስት ቀናት የአቅም ግንባታ ሥልጠና በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በሥልጠናው ማጠቃለያ የተገኙት የክልሉ ምክትል ዋና ኦዲተር ቶሎሣ አቡማ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የኦዲት ቅልጥፍናንና ተደራሽነትን ለማስፋት ከ2019 በጀት ዓመት ጀምሮ የዲጂታላይዜሽን አሠራር ሙሉ በሙሉ ይተገበራል።
ለዚህም የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኦዲተሮች ማኅበር ያወጣውን መሥፈርትና ደረጃ መሠረት ያደረገ አዲስ የክዋኔና የፋይናንሺያል ኦዲት ማንዋል ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ሥልጠናውም የኦዲት አገልግሎቱን ዘመናዊ፣ ሙያዊ እና በዓለም አቀፍ መርሆች ላይ የተመሠረተ የለውጥ ጉዞ በክልሉ ለማስጀመር ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የኦዲት አሠራርን ከወረቀት ንክኪ በማላቀቅ የኦዲት ሥነ-ምግባርን ለማክበርና ግልጽነትን ለመፍጠርም ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ኦዲት የሚደረጉ መሥሪያ ቤቶች ቁጥርና የመንግሥት በጀት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፣ ይህንን ሊመጥን የሚችል የዲጂታላይዜሽን አሠራር መዘርጋቱን ምክትል ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል።
ይህም ኦዲተሮች ሥራቸውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያከናውኑና የኦዲት ውጤት ጥራት እንዲኖረው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የፋይናንስ ኦዲት ዳይሬክተር እንዳልካቸው ታደሰ፤ ሥልጠናው በፍጥነት እየተለወጠ ካለው ዓለም አቀፋዊ የቴክኖሎጂ ሁኔታ ጋር ራስን ለማብቃት ገንቢ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ሌላው የሥልጠናው ተሳታፊ አቶ ጢቄ አብዲሳ በበኩላቸው፣ የኦዲተር ሙያ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን ከብክነት መጠበቅ በመሆኑ ይህንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ሥልጠናው ዘመኑን የዋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ገረመው አስፋ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ አዲሱ ማንዋል የኦዲት ሥራን ከኋላ ቀር አሠራር ለመውጣትና የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል ጠንካራ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።