በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ የሥራ ባህል እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ የሥራ ባህል እያሳደገ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ የሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ የሥራ ባህላቸው እንዲቀየር አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተጠቃሚዎች ገለጹ።
በከተማዋ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተፋጠነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት የተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎችን አካቶ እየተገነባ መሆኑም ተመላክቷል።
በልማቱ በሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ኤርሚያስ ዳዊት እና ማለዳ ማቴዎስ በከተማው የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
በልማቱ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የተናገሩት ወጣቶቹ፣ በዚህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ምሽት ጭምር በመስራት የሥራ ባህላቸው እየተቀየረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሠርተው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን እየደገፉና የራሳቸውን ጥሪት ለማፍራት እያገዛቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱን እያከናወነ የ ሚገኘው ስራ ተቋራጭ ባለቤት አቶ ከበደ ተካ በበኩላቸው፣ የልማት ስራውን ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ቀንና ምሽት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅንጅት እየተከናወነ ባለው የመጀመሪያ ዙር የወንዝ ዳርቻ ልማት ለ70 ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፣ ልማቱ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የህብረተሰቡን የሥራ ባህል በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተቀናጀ መሠረተ ልማት አቅርቦት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አስራት ዳዊት በበኩላቸው የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ልማቱ በሁለት ሄክታር ላይ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው አምፊ ቴአትር፣ ፋውንቴኖች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ እንዲሁም የተለያዩ መዝናኛና ማረፊያ ቦታዎች እንደሚኖሩት አስረድተዋል።
የሥራ ተቋራጩ በውሉ መሰረት ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ፈጥኖ ለማጠናቀቅም ቀንና ምሽት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለልማት ሥራው ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የተያዘ ሲሆን ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ የከተማዋን ገጽታ እንደሚቀይረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የቱሪስት ፍሰትን ለማሳደግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና የከተማዋን ገቢ ከማሳደግ አንጻር ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ሥራው በልዩ ትኩረት እየተመራ ይገኛል ነው ያሉት።