የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት ከትራንስፖርትም ባለፈ ለንግድና ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት ከትራንስፖርትም ባለፈ ለንግድና ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር ከትራንስፖርትም ባለፈ ለንግድና ኢንቨስትመንት ትልቅ እንደሚሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የክልል ኤርፖርቶች ፋሲሊቲ ኃላፊ ተወልደ ግርማይ ገለጹ።
አየር መንገዱ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ የሚያደርገውን የቅድመ ምረቃ በረራ በዛሬው እለት ጀምሯል።
ኃላፊው ለኢዜአ እንደገለጹት የደብረ ማርቆስና አካባቢው ህብረተሰብ የቆየ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጥያቄ በመንግስት በተሰጠው ትኩረት ምላሽ አግኝቷል።
በዛሬው እለትም የቅድመ ምረቃ በረራ መጀመሩን ተናግረው በተለያዩ አካባቢዎች የዜጎችን የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ፍላጎት የማሳለጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው አገልግሎት መጀመሩ ለአካባቢው ከትራንስፖርትም ባሻገር ለንግድና ኢንቨትስመንት እንዲሁም ለቱሪዝም ሴክተሩ ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመስገን፤ የደብረ ማርቆስና አካባቢው ህብረተሰብ የአየር ትራንስፖርት የረዥም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ትልቅ ደስታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩም የከተማውንና የአካባቢውን የኢንቨስተመንት፣ የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማፋጠን የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው የአየር ትራንስፖርቱ ለዘመናት የነበረውን ፍትሃዊ የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በበረራው ከተሳተፉት መካከል አቶ ባየ ገሰሰ እና ወይዘሮ ቃልኪዳን በረከት አየር መንገዱ በረራ በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢውን ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ መሰረት አድርጎ መንግስት ፈጣን ተግባራዊ ምላሽ በመስጠቱም እናመሰግናለን ብለዋል።