ቀጥታ፡

የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነትን ይበልጥ ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች እየተተገበሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነትን ይበልጥ ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች እየተተገበሩ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በጤና ክብካቤ ጥራትና ደህንነት ሰርተፊኬሽንና አክሪዲቴሽን ፕሮግራም ትግበራ ዝግጁነት ላይ ያተኮረ በተግባር የተደገፈ የልምድ ልውውጥና የመማማሪያ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አባስ ሐሰን እንደገለጹት፤ መንግሥት ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሁም ተደራሽነቱ የሰፋ የጤና አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡


 

ባለፉት ዓመታትም የጤናውን ዘርፍ ውጤታማነት ማረጋገጥና የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነትን ማሻሻል የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞችን ቀርጾ ወደ ተግባር ማስገባት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት የተሻለ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡበትን አቅም ለመገንባት ከአጋርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የአክሪዲቴሽን ፕሮግራሙን በተመለከተም ከኢትዮጵያ ስታንዳርድ ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን ስታንዳርዶችንና የትግበራ ማዕቀፎችን ሲያዘጋጁ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ፣ ተቋማቱ ወደ አክሪዲቴሽን ሥርዓት እንዲገቡ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ 32 የሚሆኑ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት የአክሪዲቴሽን ሥርዓቱን ትግበራ እንዲጀምሩ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ አምስት ዓመታት በርካታ የጤና ተቋማትን ወደዚህ ሥርዓት ለማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡


 

የኢትዮጵያና ምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ፣ መድረኩ የጤና ተቋማትን የአገልግሎት ጥራትና ደህንነት አቅም ለመገንባትና አፈጻጸማቸውን ገምግሞ ዕውቅና ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወክላቸው 31 ሺህ የግል የጤና ተቋማት ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ሕክምና እንዲሰጡ ከጤና ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ተቋማቱ ወደ አክሪዲቴሽን ትግበራ እንዲገቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ፣ በዘርፉ እውቅና ለሚያገኙ ተቋማት የሚሰጠውን ማበረታቻ የሚወስን ብሔራዊ የአክሪዲቴሽን ፍኖተ-ካርታ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም