በአማራ ክልል የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ኢንቨስትመንትና ቱሪዝምን እያነቃቃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ኢንቨስትመንትና ቱሪዝምን እያነቃቃ ነው
ወልድያ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የክልሉ ከተማና መሰረት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ከተማና መሰረት ልማት ቢሮ ክልላዊ የኮሪደር ልማት ልምድ ልውውጥና የግምገማ መድረክ በወልድያ ከተማ ተካሂዷል።
የቢሮ ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የክልሉ ከተሞችን ለነዋሪዎች፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በተለይም የመኪና፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ እንዲሁም የመዝናኛ የአረንጓዴ ስፍራና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አካቶ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማፋጠን መሰረት እየጣለ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ጠንካራ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ማዕከላት መፈጠራቸውን ገልጸው፤ ይህም ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት መነቃቃት ታላቅ ተስፋ ይዞ መጥቷል ብለዋል።
ባዛሬው የልምድ ልውውጥና የግምገማ መድረክም የተሻለ የሰሩ ከተሞች ለሌሎች ልምዳቸውን በማካፈል በቀጣይ ከተሞች ተቀራራቢ እድገት እንዲያስመዘገቡ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርጫት ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ደሳለኝ በበኩላቸው ከተሞችን በኮሪደር ልማት ለማስዋብና ገጽታቸውን ለመቀየር የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
ልማቱ የከተሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቀስቃሴ ከማሳደግ ባለፈ የገጠሩን እድገት ለማፋጠን እንደሚያስችለም አመልክተዋል።
የባህር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በበኩላቸው፣ በባህር ዳር የተገነባው የኮሪደር ልማት የጣና ሐይቅን ጸጋ የገለጠና የከተማዋን ውበት ይበልጥ ያደመቀ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደሩ ልማቱ የተሽከርካሪ፣ የሳይክልና የእግረኛ መንገድ፣ የመዝናኛ ስፍራ፣ የአረንጓዴ ሰፍራና ሌሎች ልማቶችን ማካተቱን ጠቁመው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የከተማና መሰረት ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ በጎንደር የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለቱሪዝም እንቅስቃሴና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
በተለይ የፋሲል ግንብን፣ የሰሜን ተራሮችንና ሌሎች የመስህብ ስፍራዎችን ሊጎበኙ የሚመጡ የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
ልማቱ የቀጣዩን ትውልድ እድገት ጭምር መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመው "መድረኩም ልምዳችንን ለሌሎች ከተሞች ለማጋራትና ክፍተታችን ለመሙላት ያስቻለ ነው" ብለዋል።
በኮሪደር ልማት ደሴ ከተማን ማስዋብና ማሳመር ተችሏል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ናቸው።
በመድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልል፣ የከተማና የዞን አመራሮች ተሳትፈዋል።