ቀጥታ፡

በክልሉ ስልጤ እና ሀላባ ዞኖች በመኸር ወቅት ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ይለማል

ወራቤ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ እና ሀላባ ዞኖች በ2018/19 የመኸር ወቅት ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማ ተገለጸ። 

በመኸር እርሻ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኖች ግብርና መምሪያዎች እንደገለጹት ለመኸሩ የግብርና ልማት ሥራ አስፈላጊውን የግብርና ግብአት በማሟላት የሰብል ልማት ስራዎችን ለማከናወን ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል።      

የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙበራ ከማል እንደገለጹት በዞኑ በ2018/19 በመኸር ወቅት የግብርና ልማት ሥራ ከ104 ሺህ 380 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል።

በአዝርዕትና በሆልቲካልቸር ሰብሎች ከሚለማው መሬትም ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።

ለመኸር ወቅት የግብርና ልማት ሥራ ከ306 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዶ 141 ሺህ 387 ኩንታል ማሰራጨት መቻሉን ጠቅሰው፣ ቀሪውንም በቀጣይ ጊዜያት የማሰራጨት ሥራ እይከናወናል ብለዋል።

በዞኑ በመኸር ወቅት ከሚለማው ማሳ አብዘኛው በሜካናይዜሽን እርሻ ትራክተር በመጠቀም በክላስተር እንደሚለማ ጠቁመው፤ ይህም አቅምን አሟጦ በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን ያግዛል ብለዋል።

በተመሳሳይ የሀላባ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዞኑ ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሀጂ ኑርዬ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ለመኸር ወቅት ግብርና ልማት አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው።

በዘንድሮ የመኸር ወቅት ከ28 ሺህ 140 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ1 ሚሊዮን 546 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

ለዚህም ስኬት ከ130 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የዳፕና ዩሪያ ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም