ቀጥታ፡

የቱለማ ገዳ ሥርዓት የ71ኛው ዙር የስልጣን ሽግግር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ የቱለማ ኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የ71ኛው ዙር የስልጣን ሽግግር 'ዳካ ኮራ' በተባለ ልዩ ስፍራ እየተካሄደ ይገኛል።

የስልጣን ርክክቡ ማጠቃለያ በነገው ዕለት 'ዳካ ኮራ' በተባለ ልዩ ስፍራ የስልጣን ወይም የአለንጋ ሽግግር መርሃ ግብር የተለያዩ አካላት በተገኙበት ይካሄዳል።

የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ለብዙ ዘመናት የዘለቀና ዓለም ያደነቀው የማይዳሰስ ቅርስ ሲሆን፣ ይህ ሥርዓት የማኅበረሰቡን ባህል፣ እሴትና ሥነ-ምግባር ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሻገር ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጣ ነው።

የተለያዩ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ገዳ፤ ሰላምና እርቅን የሚያሰፍን፣ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ የሚያጠናክር፣ ማንነትንና ባህልን የሚጠብቅ፣ እኩልነትን የሚያረጋግጥ እንዲሁም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ለትውልድ የሚያስተምር ሥርዓት ነው።

ይህንኑ መሠረት በማድረግ፣ በአሁኑ ወቅት የቱለማ ገዳ ሥርዓት የ71ኛውን ዙር የሥልጣን ሽግግር ከ'ገዳ ሜልባ' ወደ 'ገዳ ሙደና' ለማስተላለፍ የተለያዩ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓቶች በ'ዳካ ኮራ' የባህል ስፍራ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህ ሥርዓት ላይ ሥልጣን ለሚረከቡት አካላት ቦኩ ወይም የሥልጣን ማሳያ የሆነው በትር እና አለንጋ ይረከባሉ።

በስልጣን ሽግግሩ ባህላዊ ስርዓት ላይ ባህላዊ ግብዣዎች፣ ምርቃት፣ የሕዝባዊ ባህል ዜማዎችና ውዝዋዜዎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ የኦሮሞ ሕዝብ አዲሱን አባ ገዳ በደስታ የሚቀበል መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም