በምዕራብ ሸዋ ዞን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ የማር ምርት እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ የማር ምርት እያደገ መጥቷል
አምቦ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ለንብ ማነብ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ የማር ምርት እያደገ መምጣቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በጽህፈት ቤቱ የንብና ሐር ልማት ባለሙያ የሆኑት ብርሃኑ ለችሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዞኑ የንብ ማነብ ዘርፉን ለማዘመን በየደረጃው በተደረገው ሰፊ ጥረት የማር ምርቱን ማሳደግ ተችሏል።
በተለይም በዞኑ በሚገኙ 23 ወረዳዎች በተካሄደው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ፣ በርካታ ወጣቶች በዘርፉ ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የማር ምርቱን ይበልጥ ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች መሰራጨታቸውን ጠቁመው ባለሀብቶችም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህም በዘርፉ ለተሰማሩ 200 ሺህ አርሶ አደሮች ተጨማሪ ገቢ ከመፍጠሩ በላይ፣ ህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በገበያ ላይ እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 10 ሺህ 340 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት 11 ወራት ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
ይህ ምርት የተሰበሰበው ከ851 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች መሆኑን ጠቅሰው፣ የተገኘው የማር ምርት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ220 ቶን ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።