ቀጥታ፡

ሀዋሳን የቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ማዕከል የማድረግ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ ሀዋሳ ከተማን በማልማት የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከልነቷን ይበልጥ ለማሳደግ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።


 

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ መንግስት ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የኮሪደርና የመዳረሻ ስፍራዎች ልማት ተጠቃሽ ናቸው።

በሀዋሳ ከተማ በተከናወነው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ አጉልቶ ማውጣት ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዚህ ወቅት የሀዋሳ ፍቅር ሐይቅን ለማልማት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የሐይቅ ዳርቻ ልማቱ የሀዋሳ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን በመሆኑ፣ ሁሉም አካላት ለስኬቱ እንዲረባረቡ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በሐይቅ ዳርቻ ልማቱ ከሚገነቡ የመዝናኛ ማዕከላት በተጨማሪ፣ ዘመናዊ የትራንስፖርትና የመዝናኛ ጀልባዎችን በማስመጣት ባለሀብቶች እንዲሳተፉም ጋብዘዋል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ የሀዋሳ ወዳጆች ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።


 

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፣ የሐይቅ ዳርቻ ልማቱ ከተማዋን ከብክለት ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማውረስ የዲዛይን ስራ ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በከተማዋ እስካሁን ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት የተከናወነ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የማልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአጠቃላይ 12 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሐይቅ ዳርቻ ልማት የከተማዋን ውበት ከማሳደግ ባለፈ፣ ኑሯቸውን በአሳ ማስገር ስራ ላይ የመሰረቱ ነዋሪዎችን ህይወት ለመለወጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነውም ብለዋል።

ዛሬ የዚህ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር በይፋ የተጀመረ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን በስድስት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ ይሰራል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ ዘመናዊ ሬስቶራንቶችና ሱቆችን፣ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን፣ የመመልከቻ ማማዎችና የአሳ ማስገሪያ ስፍራዎችን፣ የህዝብ መሰብሰቢያ ሰገነቶችን፣ የጎርፍ ውሃ ማጣሪያ ስርዓትን እንዲሁም የሐይቅ ዳርቻ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም